Saturday, March 26, 2016

ፍትህ በ ወያኔ ዘመን
ፍትህ (justice)፣ በኢትዮጵያ ፍትህ ደብዝዛለች። ደብዳቢውና ተደብዳቢው ፖሊስ ጣብያ ቢሄዱ ተደብዳቢው ይታሠራል። ዘራፊና ተዘራፊ ሸንጎ ፊት ቢቀርቡ ተዘራፊው ተሸማቆ ከእልፍኙ በአፋጣኝ እንዲወጣ ይደረጋል። ዳኛና ጠበቃ የጥቅም ትሥሥር አድርገዋል። ፍርደ ገምድል ዳኛው የባለጉዳዩን ሳይሆን የጠበቃውን እጆች ያያል። ደህና ጉቦ ሰጪ ጠበቃ ዝናን ያተርፋል፣ በርካታ ደንበኞች ያፈራል። ለፍትህ የቆሙ ጠበቆች ደግሞ ሥራ ፈተዋል። "ፍትህ ይስፈን" እያሉ ሲጮኹ ሙሰኛው ዳኛና መሠሪው ጠበቃ ይሳለቁባቸዋል። ፍትህ በኢትዮጵያ እጅግ ተረግጣለች። ታድያ በአቋራጭ ለመክበር ኢፍትሃዊ ነገሮችን ሳይፈሩ መፈጸም እየተለመደ መጥቷል። በኢፍትሃዊ አሠራሮች ልምድን የቀሰሙት ደላሎችና አቀባባዮች የምክር አገልግሎት ይሰጣሉ። እነርሱ ለዳኞችና ጠበቆች ሐሰትን አደልቦ እንደምን ማሸነፍ እንደሚቻል ህግን ሳይፈሩ፣ ሰውን ሳያፍሩ ምክር ያካፍሏሉ። ክፉዎች የምክር አገልግሎት በሚሰጡባቸው ቢሯቸው ውስጥ የፍትሃብሄር ህግና መጽሃፍ ቅዱስ ሁለቱም ጠረቤዛው ላይ ተቀምጠዋል። አይ ዘመን!