Tuesday, January 17, 2017

ለምን ይዋሻል?- ለወያኔ ጋዤጠኖች ግንዛቤ መስጫ ትንሽ ጽሁፍ [ከ ሚኪያስ ግዛው]

ለምን ይዋሻል?- ለወያኔ ጋዤጠኖች ግንዛቤ መስጫ ትንሽ ጽሁፍ [ከ ሚኪያስ ግዛው]

ፖለቲካ ብዙ ኃይልና እንቅስቃሴ ነች – አዲሱን ሕዝባዊ የፖለቲካ ሰነድ ሕዝቡና መሪዎቹ ያዘጋጁ From MG

ፖለቲካ ብዙ ኃይልና እንቅስቃሴ ነች – አዲሱን ሕዝባዊ የፖለቲካ ሰነድ ሕዝቡና መሪዎቹ ያዘጋጁ
From MG


ብዙ ሰዎች ፖለቲካ ውስጥ ይሳተፋሉ። ላንዳንዱ ፖለቲካ ዝና ነች። ላንዳንዱ የገንዘብና የገቢ ምንጭ ነች። ላንዳንዱ ወደ ሥልጣን መወጣጫ ነች። በእርግጥ መላ ሕይወቱን ለትክክለኛ ፖለቲካ የሠጠ፣ ሕዝብ ሲራበ አብሮ የሚራብ፣ ሕዝብ እየታረዘና እየተሰደደ ተመችቶት የማይተኛ ሃቀኛ ሰው አይታጣም። ይህ ዓይነቱ ሰው ምስክሩ ኑሮው ነው። እውነተኛውን ፖለቲከኛ ሰዎች አይተዉት ያውቁታል፣ ይከተሉታል። ስሜትን የሚያራግበውንም ብዙ ሰዎች ይከተሉታል። ግራ የገባት ነፍስ መፍትሄ አምጭ የመሰላትን ሁሉ ትከተላለችና።

የሁሉም ፖለቲከኞች ማዕከልዊ የሃሳብ ማጠንጠኛ ሕዝብ ነው። ሁሉም ፖለቲከኞች በሕዝብ ስም ይታገላሉ። ብልጣ ብልጦችም በሕዝብ ስም ዝናን፣ ገንዘብን ወይም ሥልጣንን ሲጨብጡ ሃቀኛ ታጋዮች ሕይወታቸው ይመሰቃቀላል። ዝናቸው፣ ገንዘባቸውና ሥልጣናቸው ግን ሕዝብ ነው። እነ እስክንድር፣ አንዷአለም፣ በቀለ ገርባ፣ ተመስገን እና ሌሎች በእስር የሚማቅቁት በርካታ የኦሮሞና አማራ ልጆች እነ መራራ ጉዲና፣ ኢንጅነር ይልቃል፣ ብሌን፣ ወይንሸት፣ አብርሃ ደስታ ንግሥት ይርጋንና ሌሎችን ጨምሮ ለራሳቸው ምቾትና ድሎት እንዲኖሩ አልተፈጠሩም። ውበታቸው ሕዝብ ነው። የሕዝቡ ስቃይ ስቃያቸው ነው። የህዝቡ ብሶት ስሜታቸው ላይ ይገለጻል። ጭንቀታቸው ለሕዝብ እንጂ ለራሳቸው ዓይደለም። ገና ሲፈጠሩ ለዚሁ ሕዝባዊ ሥራ መስዋዕት እንዲሆኑ የተፈጠሩ ናቸው። ማንም ስለፈለገ እንደ እነሱ አይሆንም፣ ስላወራና ስለጮኸ እንደ እነሱ አይኮንም። እነዚህም እነዛም እኛም እነሱም ለየቅል ነው አፈጣጠራችን። በሠላማዊ ትግል ወቅት የሠላም እጆቹን አንስቶ አምባገነኖቹን ፊት ለፊት የሚሞግተው ጀግናና በብዕራቸው ጠብታ ቀለም ብቻ ሥርዓቱን የሚያንቀጠቅጡትን ጀግኖችን ታሪክ ፈጽሞ አይረሳውም። እነዚህ ጀግኖች ዋጋቸው የሕዝብ ፍቅር ብቻ ነው። ዋጋቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድል ነው። ቢሆንም ሁሉም እንደመክሊቱ ይታገላል። ዲያስፖራውም ይሠለፋል፣ ሠልፍ ይመራል፣ ወደ ውጭ የመጣውን ባለስልጣን ያራውጣል፣ በየኤምባሲው የተሰገሰገውን ቦዘኔ ዲፕሎማት ነኝ ተብዬን ያስደነግጣል፣ በቦታው ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ባንዲራ ይተክላል። ዲያስፖራው ሬዲዮ ጣብያዎችንና ቴሌቪዥን ጣብያዎችን በገንዘቡ እየረዳ ንጹህ ዜና ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲደርስ ያደርጋል፣ ቀስቃሽ ዘፈኖችን ይለቃል። ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚወረወረው አጋዥ ትግል ይህን ይመስላል። ማንም ዜጋ አይገደልም፣ ሰውነቱ ላይ ጭረት አይታይም፣ ይበላል፣ ይጠጣል፣ ቤተሰቡን በመልካም ያስተዳድራል፣ ልጆቹን ያስተምራል፣ ይድራል፣ ይደግሳል፣ ያሻው አስረሽ ምችው ይላል። ዲያስፖራው ከላይ ስማቸውን እንደጠቀስኩት ታጋዮች አይታሰርም፣ በእሳት አይቃጠልም፣ ፌደራል በምሽት እየመጣ ቤቱን አይበረብርበትም፣ ቤተሰቡን አያጉላላበትም። መስዋዕትነት ይለያያል፣ ሁሉም በቻለው ይሠለፋል። የመስዋዕትነቱ ክብደት እንደ ተሸካሚው ትከሻ ስፋት ይለያያል።

ትግል የሚሰምረው በሕዝብ ነው። ሕዝብ ውጤታማ ነው። ሕዝብ የፖለቲካ ጠበብት ነው። “የኦሮሞው ሕዝብ ወገኔ ደም የኔ ነው” ያለው የአማራ ሕዝብ “የአማራው ወገኔ ደም የኔ ነው” የሚል ሕዝባዊ ምላሽ ከኦሮምያ አገኘ። ምሁራን የለፉለትን አንድነትና ህብረት ሕዝብ በደቂቃ ተግባራዊ ያደርገዋል። ሕዝብ አብሮት ከጎኑ ቆሞ በግንባር ቀደምነት የሚያታግለውን ጀግና ይወደዋል። ሕዝብ የጎበዝ አለቃውን ይወደዋል። በትጥቅ ትግል ወቅት ግንባሩን ሰጥቶ ሕዝብን የሚመራው ጎበዝ ደግሞ ልዩ ፍጡር ነው። እነዚህ ጀግኖች ዋጋቸው የሕዝብ ፍቅር ብቻ ነው። የቱኑም ያህል መከራና ተጽዕኖ ቢገጥማቸውም እነ አበራ ጎባውና ጓደኞቹ ሕዝቡን አልተዉትም። አበራ አርማጭሆን የድል ሜዳ አደረጓት አርማውን ለጓደኞቹ አውርሶ አሸለበ። እንዲህ እንዲህ ዓይነት ጀግኖች ናቸው የኢትዮጵያ ጉዳይ ልዩ ባለቤቶች። “ኢትዮጵያ ሃገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” ተብሎ ኢትዮጵያ ዳግም አይቃኝባትም። ሕዝቡ ሁሉንም ተረድቷል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱ የሚቀርጸው አንድ የትግል ማኒፌስቶ ያስፈልገዋል። የአርባ ዓመቱ የግራ ክንፉ የትግል ዘይቤና የደደቢቱ ማኒፌስቶ አጥፊና ትውልድን ገዳይ አንድነትን አጨናጋፊ ነው። እነዚህኑ የግራው ክንፍ ፖለቲካ በደርግ ዘመን ለአስራ ሰባት ዓመት በወያኔ ዘመን ለሃያ አምስት ዓመት ባጠቃላይ ለአርባ ዓመት በተግባር አይተን ፈትነናቸው እርባና ቢስነታቸውን ሙሉ በሙሉ አረጋግጠናል። ይህ ትውልድ፣ ሃገር ቤት መከራውን የሚያየው ትውልድና ከጎኑ ያልተለዩት መሪዎቹ ራሳቸው ወደፊት ኢትዮጵያ የምትመራበትን ሠነድ በህብረት ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ዛሬ የአማራውና ኦሮሞውን ትግል ተቀናጅቶ የወያኔው ከፋፋይ ማኒፌስቶ መቀዳደዱ ሕዝቡ የደረሰበትን የንቃት ደረጃ ያሳያል። ፖለቲካ ብዙ እምቅ ኃይልና እንቅስቃሴ በመሆኗ ሕዝቡ የራሱን ኢትዮጵያዊ ሠነድ ማዘጋጀት ይችል ዘንድ ላገሪቱ የወደፊት ዕጣ፣ ሠላምና መረጋጋት፣ እድገትና እርምጃ ራዕይ የሌላቸው ምሁራን ወይንም ፖለቲካንና ተግባርን አዛምዶ ማየት የማይችሉ የግራው ትግል ዘይቤ የወለዳቸው ሰዎች ጣልቃ መግባቱን ትተው ይህን ሃገራዊ ኃላፊነት ለባለቤቱ ለሕዝቡ ቢተዉለት መልካም ነው።

ሁሉም ባይሆኑ እንኳን ያለፈው የግራ ክንፍ ፖለቲካ በርካታ ልታይ ልታይ የሚሉ፣ ዝናንና ገንዘብን ብቻ የሚያፈቅሩ ሰዎችን ኮትኩቶ አሳድጓል። ይህ ብቻ አይደለም የግራ ክንፉ ፖለቲካ ብዙ ኢሰብዓዊ ግለሰቦችን፣ ኢትዮጵያ ወደብ የለሽ እንድትሆን ያሴሩ፣ ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ ተከፋፍሎ በዘርና ቋንቋ እየተለያየ እንዲተላለቅ መርዝ የቀመሙ፣ ኢትዮጵያ ማዕድኖቿ በውጭ ባለሃብቶች እንዲመዘበርና ሕዝቧ ከድህነት እንዳይወጣ ክፋትን የወጠኑ፣ ኢትዮጵያውያን ድህነቱ ጎድቷቸው ልጃገረዶችን በየአረብ ሃገሮች እንዲሰደዱ ያደረጉ ጨካኝ፣ ሕጻናት በዝሙት እንዲወድቁ ያደረጉ ግፈኛ ግለሰቦንና ሌሎች በርካታ ሊጠቀሱ የሚችሉ ዘግናኝ ስቃዮችን የፈጠሩ ሰዎችን እንደ አሸን አፍልቷል። በግራው ክንፍ ፖለቲካ ትግል ስም ሻዕቢያና ወያኔ ሕዝቡ ውስጥ ተደብቀው መልሰው ሕዝቡን ለስደት፣ እርዛትና ውድቀት ዳርገውታል። አዲሱን ሠነድ የኢትዮጵያ ሕዝብና አብረውት መከራውን የቀመሱት መሪዎቹ ያዘጋጁ። ሠርጎ ገቦች፣ ገዳዮችና አሽቃባጮች ተዉ ሊባሉ ይገባል።