የአማራው ለብቻው መደራጀት ኢትዮጵያዊነትን ያዳክማል?
አንድ ወቅት ላይ አፍቃሪ ወያኔ የሆነው የኢትዮጵያ ፊርስት ድረገጽ አዘጋጅ ቤን የተባለው ጋዜጠኛ አቶ መለስንና አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ቃለመጠይቅ አቅርቦላቸው ነበር። አቶ መለስን እንዲህ ሲል ጠየቃቸው።(ቃለ መጠይቁን ስለረሳሁት ሃሳቡን እንጂ ቃል በቃል ላስቀምጠው አልችልም)። "እንደው ኦሮም ኦሮሞ ሲባል ይለጠጥና ኢትዮጵያዊነትን አያዳክምም?" እርሳቸው ሲመልሱም "አያዳክምም - ኦሮሞው በኦሮሞነቱ ማንነቱ ሲከበርለትና እውቅና ሲሰጠው እንደውም ኢትዮጵያዊነት ያጠናክራል" አሉ። በሌላ ጊዜ ደግሞ አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ጠየቃቸው። "እንደው ይህ በዘር በዘሩ መደራጀት ኢትዮጵያዊነትን አያላላም፣ አያፈርስም?" እሳቸውም እንደ አለቃቸው ሲመልሱ "አያዳክምም - ለምሳሌ እኔ ሲዳማ ነኝ፣ ሲዳማነቴ ሲታወቅልኝና ማንነቴ ሲከበርልኝ ኢትዮጵያን እወዳታለሁ። ስለሆነም ኢትዮጵያዊነት ይጠናከራል"። ሁለቱም መልሳቸው ላይ ማንነት (identity) የምትለዋን ጽንሰ ሃሳብ አንስተዋል። ማንነታቸውን ያወላገደባቸው አማራ ነው ወይንም ሁሉንም ገዥዎች አማሮች ናቸው ለማለት ነው። ይህ የተሳሰተ ፍልስፍና፣ ወደ ስልጣን ላይ ለመውጣት የተፈበረከ፣ ይህ እኩይ ፍልስፍና ነው አማራውን ያስጠቃው። ወያኔና ሻዕቢያ የሁሉም ዘር ጠላት አማራ ነው ሲሉ ለልጆቻቸው እያስተማሩ በምስኪኑ አማራ ላይ የግፍ ጣታቸውን ቀሰሩበት። አማራው የተሳለቀበትና ማንም እየተነሳ የሚያንቋሽሸው በዚህ ፍልስፍና፣ እዛው ደደቢት ውስጥ በተቀመረው የተሳሳተ ርኩስ ንድፈሃሳብ ነው።