Monday, September 28, 2015

“ደረቅ ራዕይ” – “ደረቅ ትግል” | Zehabesha Amharic

“ደረቅ ራዕይ” – “ደረቅ ትግል” | Zehabesha Amharic

"ደረቅ ራዕይ" - "ደረቅ ትግል"
ሚኪያስ ሙሉጌታ ግዛው ከኖርዌ
ሠማይ ጠቅስ ሕንፃዎች ተደርድረዋል ይባላል። ሠፊው ጎዳና የሠማዩን አድማስ አቋርጧል ይባላል። ወንዙ
ተገድቦ ውሃው ተንጣሎ ተኝቷል ይባላል። ማዶ ከተራራው ሥር ዘመናዊ የእርሻ ልማት ይታያል ይባላል።
የእድገቱ አሃዝ ጨምሮ የሕዝቡ ኑሮ መሻሻሉን የሚዘግብ ዶኩሜንተሪ ፊልም በቴሌቪዥን ይታያል። የአቶ
መለስ ራዕይ ሠምሯል ማለት ይሆን? - ግናስ ሀገሬ ኢትዮጵያ ምን ነካት? – ምነው ኩርምት አለች? – ምነው
ገጿ ደበዘዘ?
የአቶ መለስ ራዕይ ሉዓላዊነቷን ያስደፈረ፣ ኅልውናዋን የተፈታተነ፣ ታሪኳን ያንቋሸሸ "ደረቅ ራዕይ" ስለነበር
ነዋ። እምዪ ኢትዮጵያ ምነው ታድያ ኩርምት አትል? ምነው ገጿ አይደበዝዝ`? ራዕዩ የሕንድና የአረብ
ከበርቴዎችን ያስፈነጠዘ፣ ሼሁንና ሎሌዎቹን ያወፈረ፣ የቅኝ ገዢዎችን ምኞት ያሳካ፣ በርካታ ቀን የሰጣቸውን
ባለስልጣናትና ዘመዶቻቸውን ያባለገ ራዕይ ነበር። በአለም ባንክ ርዳታ የተነጠፈው ጎዳና ረጅም - ግን ደረቅ
የሙስናውንና የኤፈርቱን የዘረፋ ሸቀጥ በተሸከሙ ከባድ መኪኖች የተጨናነቀ ጎዳና ነው። በየመስኩ
የተንጣለሉት ሌብነትና ጉቦ ወለድ ፋብሪካዎቹ የሕዝቡን ኑሮ አላሽቀውታል። ራዕዩ ሃይማኖትን ሳይቀር
የተፈታተነ ሕዝብን ያጠወለገ የክፋት ምንጭ ነበር። ዛሬ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ቀድሞ ተንሰራፍቶ የነበረው
ሙስና ገሃድ ወጥቶ ሙስናውያኑን እያባረረ ነው። በቅርቡ በኦሮምያና ትግራይ ክልሎች ባሉ ትልቁ የሙስና
ዋሻ የመሸጉ ሁሉ ሙቅ ውሃ እንደተደፋባቸው አይጦች ይራወጣሉ። የስባዓዊ መብት ጥሰቱ ይቁም (Stop
human rights violation)፣ አምባገነንነት ይውደም (Down with Dictatorship)፣ ሙስናው ያብቃ (Stop
Corruption)፣ የሚሉ ሰላማዊ መፈክሮች ይዘን ስለወጣን ለስደት የዳረጉን ከቀበሌ እስከ መንግስት አመራር
ያሉ ሁሉ ነገ ተጠያቂዎች ናቸው።
በእርግጥ ሙስናው ያደለባቸው አምባገነኖች ደረቅ ተቃውሞን አይፈሩም። ደረቅ ከደረቅ ቢጋጭ ለውጥ
እንደማይመጣ ተንኮሉን ጫካ እያሉ አውጠንጥነውታል። አምባገነኖቹ ደረቅ ወሬን፣ ደረቅ ጽሁፍን፣ ደረቅ
ጩኸትን፣ ደረቅ አመጽን አይፈሩም። ደረቅና ውሸት ጋጋታዎች የእድሜአቸው ማራዘምያ ኪኒኖች ናቸው።
ወያኔነዎቹ በበርሃ ላይ ድንገት ፍልቅ እንደምትለው ምንጭ ርጥብ ነገርን ከተመለከቱ ነው ክው የሚሉት።
ታድያ መልሰው እስኪያደርቋት ድረስ እንቅልፍ አይወስዳቸውም። ዓይነተኛ ባህርያቸው ይህ ነው። ወያኔዎች
እስክንድር ነጋንና አንዷለምን እንደ ጦር ይፈራሉ። ወደፊት ሌላ እስክንድርና አንዷለም ዓይነቶች
እንዳያብቡም ነው ዛሬ በሰማያዊ፣ በአንድነትና በመኢአድ ፓርቲዎች ላይ ከፍተኛ ወከባ የሚያደርጉት። አቶ
መለስን ትንሿ የእስክንድር የብዕር ጠብታ ለፍርሀቱ ስትዳርጋቸው - የአበበ ገላው ድምጽ ደግሞ ኃይል
አግኝቶ አንገታቸውን አስደፍቷቸው ነበር።
ዛሬ ሃገሬን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን የቀሰፈው ትልቁ በሽታ ፍርሃቱ እንጂ የኢሕአዲግ ብርቱነት አይደለም።
ደረቅ ትግሉ ተስፋ አስቆርጦ አድርባይነትን አስፋፍቷል። ድርቀቱ የተግባር ብኩንነቱን አስፋፍቶ "እስኪ
ልኑርበት" የሚሉ ግለሰቦችን አብዝቷል። ድርቀቱ "ቤቴን ልስራበት - ልጆቼን ላሳድግበት" የሚሉ ፈሪዎችን
አበራክቷል። እምነት ደርቃ ቤተክርስትያን ሂያጁ የትለሌ አስኪሆን ድረስ "ደረቅ ትግሉ" የአስመሳዮች ምሽግ
ሆኗል። ጸሎቶች ደረቅ ጸሎቶች ሆነዋል። ድርቀቱ የሕዝቡን አንድነትም ሆነ የተቃውሚውን የፖለቲካ ስልት
አወላግዷል። ታድያ ለዚህ ሁሉ ከንቱነት የዳረገንን አዚም ሳጤን – "በርግጥ አቶ መለስ ለካ - የደረቁ ምጣኔ
ኃብት ፈላስፋ፣ የአፈናና ስውር ግድያ መሃንዲስ፣ የታላቁ ሤራና የደረቁ ትግል ስትራቴጂስት፣ የክፉ
አደረጃጀት ስልት ቀያሽና ሕዝብ ከሕዝብ - ዘር ከዘር እሚናከስበትን መላ ጠንሳሽ፣ የመሃይማንና የደናቁርት
ስብስብ መሪና - የኃጢዓት ሥራ ዋና ተዋናይ ነበሩ" - ለማለት እደፍራለሁኝ። ብቻ ፍርዱን ለእግዚአብሔር
እንተወው።
የሚያሳዝነው ታድያ እስካሁን ድረስ በአቶ መለስ መተት ለተቀሰፈው የውስጡም የውጭውም ደረቅ ትግል
ማርጠብያ መድሃኒት አለመገኘቱ ነው። መፈክሮቻችን፣ ሰልፎቻችን፣ ስብሰባዎቻችን፣ ጽሑፎቻችን የታንክ
ጥይት ቢሆኑ ኖሮ የሕወሀት ዘመን አጭር በሆነ ነበር። እንደተዋጊ ጄቶች የፈጠኑት ድኅረ ገጾች፣ ጋዜጦችና
መጽሄቶች ቦንብ ተሸካሚዎች ቢሆኑ ኖሮ ሕወሀትና ሻዕቢያ መቀመቅ ወርደው ሕዝቦች ነጻ በወጡ ነበር።
በገቡ በጥቂት ቀናት መወገድ ስለነበረባቸው ኢሕአዲጋውያን በማውሳት ሕዝቡ - "ሳንፈልጋቸው ሀያ
ሞላቸው" – በማለት ብሶቱን አች አምና በታላቁ ሩጫ ወቅት አሰምቷል። ትግሉ እጅግ ለመዘግየቱ ከዚህ ሌላ
ምን ማስረጃ አለ?
የአቶ መለስ መንፈስ በተቃዋሚው ጎራ ሳይቀር ሰርጎ ገብቶ ተግባር በሌለው ምላሳቸው ሰብዓዊ መብት
ተገፈፈ፣ ምርጫው ተዛባ፣ ሙስና ተስፋፋ፣ ዲሞክራሲ የለም - እያሉ የሚያስተጋቡ ልሳናቸው የኢትዮጵያን
ክብር የማያውጅ ደረቅ አስመሳይ ተባባሪዎችን ሳይቀር አፋፍቷል። ባጠቃላይ "ደረቅ ትግሉ" የኢትዮጵያ
የቀድሞ ክብሯና ገናናነትዋ ዳግም እንዳይመለስ ለሚፈልጉት ምዕራብያውያን እፎይታ፣ ለኢሕአዲጎቹ እድሜ
ማራዘምያ ኪኒን፣ ለሻዕቢያ - ለኦነግና ለአልሻባብ ጊዜ መግዢያ አሞሌ ጨው እንዲሁም በዝርፊያና በወንጀል
ተጠያቂ ለሆኑት ግለሰቦች ሽፋን ሠጪ ተኩስ ከመሆን በቀር ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ አፋጣኝ መድህን መሆን
አልቻለም፣።
ልብ በሉ! ኢሕአዲጎቹን ማስወገድ ያለብን የቅኝ ገዢዎች ተባባሪዎች፣ ለሀገሪቱ ሉዓላዊነት፣ ክብርና ታሪክ
ፈጽሞ የማይጨነቁ፣ ሃገሪቱን ወደብ አልባ ያደረጉ፣ ኃይማኖትን የበከሉ፣ ሕዝቡን ለ"ስደት ሞት"ና ለ"ዳግም
ክፉ" ቀን የዳረጉ ሰው መሰል ጨካኝ አራዊቶች ስለሆኑ ነው። ይህ ደግሞ በኢንተርኔት፣ ፓልቶክ፣ ሬድዮና
ቴሌቪዥን በሚተላለፍ "ደረቅ ትግል" ብቻ አይሞከርም። ዛሬ በአቶ መለስ የሙት መንፈስ ምስል እየተመራ
በመበታተኑ ጣዕረ ሞት የሚያቃስተውን ኢሕአዲግ ገፍትረን መጣል ካልቻልን ነገ አገግሞ ለሌላ መቅሰፍት
ይዳርገናል። እንዲህ ተበታትነን፣ መስዋዕትነት የከፈሉትን ጀግኖች ገለል እያደረግን፣ ለወንጀለኞችና ለበታኞች
ፍሪዳ እያረድን፣ የጓደኝነቱን፣ የአበልጅነቱን፣ የሚዜነቱን "ስውር አብዮት" በየመሸታው እያጠናከርን - በደረቅ
ትግሉ ብቻ ተቃውሞን ከቀጠልን የሀገሪቱ መጪ እድል መገነጣጠል፣ መፈረካከስ - የሕዝቡ ዕጣ ደግሞ
መራብ መታረዝ ብሎም - የ"ስደትን ሞት" - እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ መቀበል ብቻ ነው።
ወያኔን ለማስወገድ መፍትሄው አንድ ብቻ ነው። መፍትሄው የመንፈስ ፅናት ነው። እንደ አለፈው ትውልድ
የጠላት ፈረስና ሰረገላ ማኅተማቸውን ሳያላላ፣ በእግዚአብሄር ኃይል ራሳቸውን አበርትተው፣ በባህሩ በደረቅ
መሬት፣ በሸለቆና በተራራው ተሰማርተው የሃገሬን ቁስለቷን እንደ ሻሩላት ጀግኖች ምሳሌ ለመሆን አስቀድሞ
የፅናቱ ቅባ ቅዱስ እንዲነካን በይቅር ባይነትና ፍቅር ዳግም መደራጀት ይኖርብናል። ፅናት አቋምን
ትወልዳለች። ውጤት የምናመጣው የሕዝብ ወገን የሆንን ሁሉ በሕብረት ተደራጅተን እንደ አንድ ሰው ሆነን
ስንታገል ብቻ ነው።
አለበለዝያማ ጽናትን የሚያጎለብተውን፣ የጀግኖቹን ፈለግ መከተሉን ትተን፣ ጋጋታና አጀብ ስናበጃጅ ዘመኑ
በከንቱ እንዳያልፍ እንጠንቀቅ። የመስመር ልዩነት የሌላቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች በቶሎ ወደ አንድነቱ
መምጣት አለባቸው። ለሃገሪቱ ርጥብ ራዕይ ያላቸው ድርጅቶች ሁሉ መቀራረብ አለባቸው። ኢትዮጵያ
የምታገግመው ከትግሉ ሜዳ በተለያዩ ምክንያት የራቁትን ጀግኖቿን በፍቅር ተማጽኖ ትግሉን እንደገና
እንዲቀላቀሉ ሲደረግ ነው። ማዕከላችን ኢትዮጵያ ነች። ሁላችንም ለኢትዮጵያ እናስባለን። ልዩነታችን
ውበታችን ነው። አንድነታችን አምባገነንነትን ያንበረክካል። ሙስናን ያጠፋል። ኢትዮጵያ የሰው ልጆች መብት
የማይረገጥባት ሀገር ትሆናለች።
አምላክ ኢትዮጵያን ይጠብቃት።
አድራሻዬ michyas.ethio@yahoo.com ነው።

Ethio peace and politics : "ሕዝባው መንግስት"፣ "ሕዝባዊ መፈናቅል" ወይንስ "ሕዝባዊ መፍረስ"ሚክያስ ሙ...

Ethio peace and politics : "ሕዝባው መንግስት"፣ "ሕዝባዊ መፈናቅል" ወይንስ "ሕዝባዊ መፍረስ" ሚክያስ ሙ...: "ሕዝባው መንግስት"፣ "ሕዝባዊ መፈናቅል" ወይንስ "ሕዝባዊ መፍረስ" ሚክያስ ሙሉጌታ ከ ኖርዌ ድሮ ከዘውዱ መገርሰስ በፊት አዲስ አበባ እንደህ እንዳሁኑ ጭንቅንቅ ያላለች...
አርበኞች ግንቦት ሰባትና ሊቀመንበሩ ዶክተር ብርሃኑ ነጋከሚክያስ ሙሉጌታ ግዛው
ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በወጣትነታቸው ዘመን እንደማንኛውም ወጣት በተማሪው ንቅናቄ የተሰለፉ፣ የኢሕአፓ የወጣቱ ክንፍ አባል በመሆንም ደርግን የታገሉ ኋላም ወደ ሱዳንና አሜሪካ የተሰደዱ የነጻነት ትግሉ አባወራ ናቸው። ዶክተር ብርሃኑ ደርግ ወድቆ ወያኔ ስልጣኑን ሲይዝ ሕዝቡን እውጭ ባካበቱት ልምድ ለማገልገል ፈቅደው ወደ ሃገራቸው ተመልሰው በዩኒቨርሲቲ ከማስተማር ጀምሮ በቅንጅት ፓርቲ ውስት በአመራሩ ውስጥ ጉልህ ተዋናይ እስከመሆን ድረስ አገልግለዋል። ቅንጅት አምባገነኑን ሥርዓት በሠላማዊ መንገድ በመታገል በአፍሪካ ምድር ለመጀመርያ ጊዜ ሕዝባዊ ምርጫ አሸናፊነቱን እንዲጎናጸፍ የበኩላቸውን አስተዋጾ አድርገው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እንዲሆኑ የተመረጡት ዶክተር ብርሃኑ ሥልጣኑን በሰላም ለማስረከብ ፍቃደኛ ባልሆነው ወያኔ ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር በእስር ቤት ተወርውረዋል። ከወራት እስር በኋላ የተፈቱት ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ወደ አሜሪካ ተመለሱ።
ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ወያኔ ስልጣኑን በሠላማዊ መንገድ ለማስረከብ ባህርይው እንደማይፈቅድለት ከተረዱ በኋላ ግንቦት ሠባት የዲሞክራሲንና ፍትህ ንቅናቄን፣ ከሌሎች ጓዶች ጋር በመሆን መሥርተው ሲያደራጁና በፋይናንስ ሲያጠናክሩ ቆይተው በቅርቡ ከአርበኞች ግንባር ጋር የተዋሃደውን የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄን ፍልሚያ ሊመሩ ወደ ኤርትራ ምድር ተጉዘዋል። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ወደ አስመራ ሲጓዙ የመን ላይ በወያኔ የተጠለፉት ሌላኛው ግንቦት ሰባትን አምጠው የወለዱ የኢትዮጵያ አንጡራ ልጅ ናቸው።
ዶክተር ብርሃኑ ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ የተለዩ አለመሆናቸውን ዘወትር ይናገራሉ። መማር ለሀገር ሕልውና ካልበጀ፣ ሕዝቡን ቀና ካላደረገ የጋን ውስጥ መብራት ሆኖ እንደሚቀር በየስብሰባው ይገልጻሉ። ዶክተር ብርሃኑን የሚያረካቸው የነጻነት ትግል እንጂ የሥልጣን መዳረሻው ወንበር ምቾት አይደለም። ይህ የዶክተር ብርሃኑ ነጋ የትጥቅ ትግሉን ለመቀላቀል ብሎም ለመምራት ወደ ኤርትራ ጉዞ በኢትዮጵያ ሕዝብ ሥልጣን ትግሉ ረዥም ጉዞ አንድ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ መክፈቱ ብቻ ሳይሆን ግንቦት ሰባት ለሕዝብ የገባውን ቃል ኪዳን ተራ በተራ መተግበሩን ይመሰክራል።
ወያኔ በሠላማዊ ትግሉ ፈጽሞ ስልጣኑን ማስረከብ እንደማይችል መረጋገጡ ሕዝቡ በአንድ ልብ የትጥቅ ትግሉን እንዲደግፍ ያደርገዋል። የአርበኞች ግንቦት ሰባት የሠሞኑ ማጥቃት ከትጥቅ ትግሉ በቀር ሌላ ፖለቲካዊ አማራጭ እንደሌለ በጽኑ ስለሚያሳይ ዳር የቆሙም ሆነ ፖለቲካ በሩቁ የሚሉ ሁሉ ሃገራዊ ድርሻቸውን ለማበርከት ይነሳሳሉ። የትጥቅ ትግሉን ለመቀላቀል ሠፊ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች ከስደቱ ውርደት ይልቅ የጦር ሜዳውን ጀግንነት ይመርጣሉ። ሳይወድ በግድ የወያኔውን ስልጣን አስጠባቂ የሆኑት የመከላከያ ሠራዊቱና የፖሊስ አባላት ሕዝባዊውን ትግል በፍቅር ይቀላቀላሉ። ሌላው ቀርቶ የሙስናው ጥቅም ተቋዳሾች የሆኑት ባለስልጣኖቹና ዘመዶቻቸው ሳይቀሩ ስህቶቻቸውን አርመው፣ የበደሉትን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀው ወያኔን አንቅረው በመትፋት የዘረፉትን የሕዝብ ሃብት በውዴታ ይመልሳሉ።  
መልካም ፖለቲካ በሰዎች አመለካከት ላይ የተንሰራፉ ብዥታዎችን ታጠራለች። ፖለቲካ አይታመንም፣ አሜሪካ ተቀምጦ ትግል የለም፣ ወዘተ፣ ዓይነቶቹ ግራ አጋቢ ብዥታዎችን እያጠሩ፣ የትጥቅ ትግሉን በማደራጀት ወያኔን መሪር የሆነ ቀውስ ውስጥ የከተተው ብሎም ከሕዝብ ወገን ከተውጣጣው ጦር ጋር እንዲላተም ያደረገው እንደነ ዶክተር ብርሃኑ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌና መሠሎቻቸው ያበረከቱት ትዕግስትንና ብስለትን የተላበሰው በሳል የፖለቲካ ሂደት ነው። ፖለቲካ እጅግ ተለዋዋጭ መሆኗ ብቻ ሳይሆን አስተማሪም ነች። በአንክሮ ለተመራመራት ፖለቲካ የትላንቱን ስህተት አጉልታ እያሳየች ወደ ተሻለው አቅጣጫ የምትመራ ምስጢራው ኮምፓስ ነች። በአንክሮ ማየት የተሳነው ደግሞ ሁልጊዜ ወደ ታች፣ ወደ ቁልቁለቱ ይጓዛል። መልካም ፖለቲካ ትክክለኛውን መንገድ ስትጠቁም ሙስና ደግሞ ልቦናን ጋርዳ ወደ ገደሉ ታዳፋለች። እብሪተኛውን ወያኔ ባዶ ያስቀረው አላዋቂ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከጀርባው ልትወርድ ያልቻለችው አታላዩዋ፣ አዘናጊዋ ሙስና ነች። ወያኔው በሙስና የገነባውን ሕንጻ አንጋጦ ሲያይ ወይም ምቾቱ በተደላደለው እጅግ ውድ ዘመናዊ አውቶሞቢሉ ሲንሸራሸር አልያም ከፍ ዝቅ በሚለው አረግራጊው በኤሌክትሪክ ኃይል በሚሞቀውና በሚቀዘቅዘው ፍራሽ ላይ እንደተኛ ሕዝባዊው ሱናሜ ከተፍ ይልበታል።
የሁለት አስር ዓመቶቹ መልካምና ሠላማዊ የፖለቲካ ክንውኖች እንዲሁም ከታሪክ ሂደት መማር ያልቻለው "የመቶ ፐርሰንቱአሸናፊው ወያኔው ግትር ባህርይ ይህን የትጥቅ ትግል ወልዷል። ፍልሚያው በግለሰቦች አስተሳሰብ ላይ ሠፍነው የነበሩትን አንዳንድ ጥርጣሬዎች አስወግዶ መላውን ሕዝብም ሆነ የፖለቲካ ንቅናቄዎችን እንዲሁም የትግል ግንባሮችን በቅጡ ያዋህዳል።
ሁሉም በጦርነት ተሠልፎ ተዋጊ ሊሆን አይችልም። ጀግንነት፣ ተጋድሎና መስዋዕት ለመክፈል ከፊት መቅደም ከእግዚአብሄር የሚበረከት ፀጋ ነው። ወታደርነት እልህ አስጨራሽ፣ ጀግንነት ደግሞ ከጽናት የምትመነጭ አኩሪ ተግባር ነች። ሁላችንም በዚህ አኩሪ ተግባር ውስጥ መሰለፍ ባንችልም እንኳን ደጀን መሆን አያቅተንም። መናቆርን፣ መጠላለፉን አስወግደን ሁላችንም ፊታችንን ወደ ጦሩ ግንባር በማዞር የሞራል፣ የቁሳቁስና የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅብናል። በአንድም በሌላም ከመሳተፍ ተቆጥቦ የነጻነቱን ትግል አለመቀላቀል ወይም ወስልቶ መቅረት በግለሰቡ ዓዕምሮ ላይ ህፍረት ሆና ተለጥፋ የምትቀር የታሪክ ጥላሸት ነች። ይህች በሁሉም መስክ ክብር የነበራት ውድ ኢትዮጵያችንን ያዋረደውን ወያኔን መፋለም ታላቅ ክብር ነው።
በአርበኞች ግንቦት ሠባት አባልነት ተመዝግበን ትግሉን የመቀላቀል እድል የተጎናጸፍን ሁሉ ሌሎችም የኛን አርዓያ ተከትለው ሃገራዊ ድርሻቸውን የማበርከቱ እድል እንዲገጥማቸው ልባዊ ምኞታችንን እንገልጻለን። በዚህም ይሁን በዚያኛው መሰለፍ፣ የነጻነት ትግሉን የሚያግዝ አንዲት ጠጠር መወርወር ወይም የሕዝቡን መሠረታዊ መብቶች የሚያስጠብቀውን ትግል ከመቀላቀል የበለጠ ሌላ ጣፋጭ ነገር የለም።
አርበኞች ግንቦት ሰባት ያሸንፋል፤ ሕዝብ ያሸንፋል፤ አምባገነንነት በትግል ይወገዳል