እነዚያ ቀያዮቹን የቻይኖች መኪኖች ገና ከሩቅ ሲያዩ ጭራቅ የመጣባቸው ያህል ልጆች ይርበደበዳሉ። ገና የሲኖ ትራኩን ድምጽ ሲሰሙ የከለላና መከታ አያያዝ ስልትን ያልተማሩት እነዚያ ጨቅሎች የሚደበቁበትን ቦታ ለመምረጥ ሲባዝኑ ይታያሉ። "ሲኖ ትራክን ገና ከሩቁ ስታዩ..." እያሉ ወላጆቻቸው ጠዋት ጠዋት የሚነግሯቸው የጥንቃቄ አወሳሰድ ምክር ትምህርቱን አስረስቷቸዋል። ይህንኑ አደገኛ ቀይ መኪና ወላጆች በዘመናቸው ካዩት ዘግናኝ ድርጊት ጋር በማመሳሰል "ቀይ ሽብር" ብለውታል።
ሃገራችን ኢትዮጵያን አንገቷን ካስደፋት ትላልቆቹ ክፋቶች መካከል የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ስግብግብነትና የኅሊና መሸርሸሩ እጅግ አሳዛኞቹ ናቸው። ሃገር የቱንም ያህል ለማች፣ በሰማይ ጥቀስ ሕንጻዎች አሸበረቀችም ሆነ ዘመናዊ መንገዶች ተነጠፉላት ሥነ-ምግባርና ግብረገብነት ከተሸረሸሩ "ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭ" ነው።
በንጉሡም ይሁን በደርግ ዘመን ሙስናና ጉቦ ቢኖርም እንዲህ እንዳሁን ሕዝቡን አላንገሸገሸም ነበር። አብዛኛው ሰው ፈሪሃ እግዚአብሄርነት በውስጡ ስላደረ በኅሊናው ይተዳደር ነበር። በደርግ ዘመን "መንጃ ፍቃድ በጉቦ አውጣ"፣ "መንጃ ፈቃድ ቤቱ ድረስ መጣለት"፣ ሲባል ሰው ወሬውን እንደ ጉድ ተገረሞ ያዳምጥ ነበር። ሰውንም ራስንም አደጋ ውስጥ የሚከት መርዝን በጉቦ መሸጥ የቴክንሽያኑን ኅሊና ቢስነት ደረጃ መገመቻ ነበር። መንጃ ፈቃድ በጉቦ መስጠት የሞት ፍርድ ያህል ነበር። ዛሬ እፍረት መሆኑ ቀርቶ ሁሉም ነገር ሙስናና ጉቦ ሆኗል። ሙስና ሞትንም ትሸጣለች። መሬት በጉቦ ይቸረቸራል። ባለገንዘብ መሬት ገዝቶ ጭሰኞች ይቀጥራል። የሠማይ ስባሪን ያህል ሹመት ተሸካሚ ግለሠብ ሕንጻ አከራይ ሁኗል። የሕዝብ አደራ የተሸከመው አገልጋይ አስመጭና ላኪ ነጋዴ ሆኗል። አለማየሁ እሼቴ ምናልባት በስድሳዎቹ መግቢያ ላይ ነው መሰለኝ፣ ባማረ ድምጹ - "ማን ይሁን ትልቅ ሰው" - በሚለው ዘፈኑ ላይ - "እባክህ አምላኬ ደጉን ዘመን አምጣ" - ሲል ለእግዚአብሄር ምልጃውን አቅርቦ ነበር። የየኔውን ዘመን ገምቶ አምላኩን የተማጸነው ከያኒ ዛሬስ ምን ታዝቧል? ምናልባት አለማየሁ እሼቴ እንደገና ቢያንጎራጉር "እባክህ አምላኬ ያን ዘመን መልሰው" ይል ይሆን? በእርግጥ የዘንድሮው ከተሻለ ያምናው ታሪክ ነበር። አለመታደል ሆኖ እንጂ "ከዘመን ዘመን አሸጋግረን" ማለት ከኋለኛው ዘመን ወደ አዲሱ ዘመን በላቀ መንፈሳዊ ጽናት፣ በተሻለ ሠላምና ብልጽግና አሸጋግረን ማለት ነው። "ልማታዊው መንግሥት" ሥነ-ምግባሩንና ግብረገብነቱን ሸርሽሮ ሁሉንም ደረመሰው።
ሲኖ ትራክ ምንም አላጠፋም። ሲኖ ትራክ በቻይና የተፈረበከ ፈጣን ጉልበታማ መኪና ነው። ጥፋቱ የሹፌሩ ነው። ጥፋቱ የአሽከርካሪው ነው። በእርግጥ ጥፋቱ የአሽከርካሪው አይደለም። ጥፋቱ የሥርዓቱ ነው። ጥፋቱ በእድሜው ለጋ ለሆነው ወጣት ወይም ሱሰኛ ካለችሎታው አራተኛና አምስተኛ ደረጃ መንጃ ፈቃድ የሚሰጠው የየክልሉ መሥሪያ ቤት ነው። ቀድሞ መንጃ ፈቃድ በትምህርት ዲግሬ ከማግኘት ያላነሰ ፈተናና ውጣ ውረድ ነበረው። ቀድሞ መንጃ ፈቃድ ለማግኘት ከሁለተኛ ደረጃ ወደ ሶስተኛ፣ ከሶስተኛ ወደ አራተኛ፣ ከአራተኛ ወደ አምስተኛ፣ ለመዝለል እጅግ ከፍተኛ ልምድንና ብስለትን ይጠይቅ ነበር። ዛሬ መንጃ ፈቃድ በጉቦ መያዝ ከጉልት በቆሎ የመሸመትን ያህል እንኳን አይከብዱም። ዛሬ ሹፌሮችንና ረዳቶችን ለይቶ ማየት አይቻልም። ሹፌሩ አራራ ይዞት ጫት ለመቃም አንዱ ሥርቻ ጎራ ሲል ረዳቱ መኪናውን ያሽከረክራል። የታክሲው አሽከርካሪ ዕቃ ለመግዛት ሱቅ ሲገባ ወያላው ሁለት ቢያጆ ሰርቶ ይጠብቀዋል። የታክሲው ባለቤት ይህን ሁሉ ጉድ አያውቁም። ቢያውቁም፣ ታክሲው የዕለቱን ገቢ ይዞላቸው እስከመጣ ድረስ ለተሽከርካሪው ደህንነትም ሆነ ለተሳፋሪዎቹ ነፍስ፣ ቅጠል ተሸክማ አስፋልቱን ለምትሻገረዋ ባልቴትም ሆነ ወደ ቄስ ትምህርት ቤት ለሚጓዙት ጨቅሎች አይጨነቁም። እሳቸውስ ቢሆን ምን ያድርጉ – ለሾፌራቸውና ረዳቱ መንጃ ፈቃዱን የሠጠው መሥሪያ ቤትን የሕዝብ ጉዳይ ካልቆረቆረው።
ሥርዓቱ መንጃ ፈቃድ አስጣጡም ላይ ሆነ የበሰለ ልምድ ያላቸው የከባድ መኪና አሽከርካሪዎችን በአግባቡ እንዲሰማሩ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረበት። ይህ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ የሚታየው የበርካታ ሰዎች ውድ ሕይወጥ መጥፋትም ሆነ የንብረት መውደም ባልተከሰተ ነበር። ሥርዓቱ ዘመናዊ መንገድን ማንጠፍ ብቻ ሳይሆን አነዳድን፣ በርጋታ መቅደምንም ሆነ በመስመሮቹ ማህል ረግቶ የመንዳትን ሥነ-ጥበብ ቀርጾ ትምህርቱን ማሰራጨት ነበረበት። ፈጣን መንገድን ሥልጣኔ ለጎደለው አሽከርካሪ"ፈንጭበት" ብሎ መልቀቅ ራሱ "ቀይ ሽብርን" ማፋፋም ነው። ሲኖ ትራኮች "ቀይ ሽብር" የተባሉት ለዚህ ነው። ከአዲስ አበባ አዳማ የተዘረጋው አውራ ጎዳና (motor way) ላይ መንዳት ከተክለ ኃይማኖት መርካቶ እየተሽለኮለኩ የመንዳትን ችሎታ ማሳያ መንገድ አይደለም። በፈጣን መንገድ ላይ ፍሬቻ ሳያበሩ መታጠፍ ወደ ሽንኩርት ተራው ተጋፍቶ እንደመግባት ቀላል አይደለም። በዘመናዊው መንገድ መንዳት "ሥልጣኔን" እንጂ "አራዳነትን" አይጠይቅም። የመንገዶቹን መስመሮች ማህል (driving field)ጠብቆ መንዳት፣ ወደ ሌላ መሥመር ለመግባት ፍሬቻ ማሳየት (turn signal)፣ እስር የተወተፈ መኪና ወይም ሞተር ሳይክል መኖር አለመኖሩን (blind spot) ማረጋገጥ፣ በጥንቃቄ የመቅደም ስልትን (take over) እንዲሁም ፍጥነትን መቆጣጠርና (speed control) ከፊት ካለው ተሽከርካሪ እርቀትን መጠበቅ (safe gap) ወዘተ፣ የመንዳት ችሎታ ብቻ ሳይሆን ሥልጣኔና (civilization) ለነፍሳት ሁሉ የመጠንቀቅ ሠብዓዊነት (humanity) ነው። በከተማ ውስጥ ለእግረኞች ቅድሚያ መስጠት ከሁሉም በላይ አስተዋይነት ነው። ምናልባት መኪና ማሽከርከር ፈቃድ ያላቸውን ዲያስፖራዎችን አሰባስቦ በአውራጎዳና ላይ አነዳድን በኤግዚቢት መንገድ የማሳየት ወርክ ሾፕ ቢዘጋጅ ጠቃሚ ይመስለኛል። ይህን ስል ካገራችን በቂ ችሎታ ያላቸው አስተዋይ አሽከርካሪዎች ጠፍተዋል ማለቴ ሳይሆን የውስጡንም የውጭውንም ልምድ መለዋወጡ ትምህርትን ከመቅሰምያ ዘዴዎች አንደኛው ነው ማሌቴ ነው። አምላክ ሀገራችንን፣ ወገናችንን ይጠብቀን፣ አሜን።