Tuesday, April 28, 2015

አርበኞች ግንቦት ሰባት መድኅን ነውሚኪያስ ሙሉጌታ ከ ኖርዌ

ሃገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት ግማሽ ምዕት ዓመታት በመከራ ውስጥ አልፋለች። ከታሪክ እንደተረዳሁት በንጉሡ ዘመን መፈንቅለ መንግስት፣ የፖለቲካ ተቃውሞዎችና አብዮት ተፈራርቀዋል። የተሻለ ሥርዓት አመጣለሁኝ ብሎ ይህንኑ መንግሥት ያስወገደው ደርግ አበሳዋን በአራት እጥፍ ጨመረው። ደርግ ከተቃዋሚዎቹ ጋር እየተፋለመ ለአስራ ሰባት ዓመታት በእብሪት ሲገዛ ብዙዎች ተገድለዋል፣ ተሰደዋል አልያም ታፍነው የሰቆቃ ሕይወት አሳልፈዋል። ዘመኑ በዲሞክራሲ እጦት ሃገሪቱ ግፍና በደልን ማስተናገዷ ብቻ ሳይሆን ጦርነቱ፣ ረሃቡ፣ ድህነቱና እርዛቱ ተጨምሮበት ኢትዮጵያን የሲዖል ምድር አድርጓት ነበር። የሃገሪቱ ችግር በዚህ አላበቃም። ግፈኛውን ደርግ በትጥቅ ትግል አስወገድኩኝ ያለው ወያኔ ላለፉት ሃያ አራት ዓመታት በስልጣን ላይ ሲቆይ የፈጸመውን ግፍና መከራ ለመናገር በሚያስቸግር ሁኔታ ስርዓቱን በዘረኝነትና በማናለብኝነት አገዛዝ ለውሶ አበሳውን በአሥር እጥፍ አሳደገው። እንደው እንዳቅሜ በሂሳብ ሳሰላው በንጉሡ ዘመን ከነበረው የሃገሪቱ ችግር በባሰ የደርግና የወያኔ ግፍ ተደማምሮ አበሳው በአስራ አራት እጥፍ ጨምሯል። አስራ አራት እጥፍ መከራን የሚያስተናግደው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ ችግር የሚላቀቅበትን መላ መፍጠር አስፈላጊ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግርን ለመቅረፍ እንዲሁም ዘረኛውን አምባገነኑን ወያኔ ለማስወገድ ሠላማዊ ትግል ዋና መፍትሄ ነበር። ሠላማዊ ትግል እንዳለፉት ዘመናት በሰው ሕይወት ላይ ጥፋት እንዳይከሰት የሚያግዝ በሳል የፖለቲካ ስልት ነው። ሆኖም ግን በጫካ ውስጥ የተፀነጸው ክፉው ወያኔ ባህርይው ይህንኑ የሰላማዊ ትግል መንገድ እንዳይከተል ይግደራደረዋል። በሕዝብ ዽምጽ በአፍሪካ ምድር ለመጀመርያ ጊዜ የተመረጠውን አሸናፊውን ቅንጅት በጦር መሳርያ አባረረው። ይህ ተገፍቶ የተባረረው ቅንጅት ነው ወያኔ በሰላም ሊያስረክብ ያልቻለውን የሕዝብ ስልጣን በጠመንጃ አፈሙዝ ሥር ተንበርክኮ እንዲያስረክብ ሊያስገድደው ቆርጦ የተነሳው። የቅንጅትን መንፈስ የተላበሰው ግንቦት ሰባት ከሰላም ይልቅ ጦርነትን አይመርጥም። ጦረኝነት ባህርይው አይደለም። ግንቦት ሰባት ፍቅር እንጂ ጥላቻን አያውቅም። ግንቦት ሰባት ጠላቶቼ የሚላቸው የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች የሉትም። ግንቦት ሰባት የሰላም እጆቹን ምን ጊዜም አይታጠፉም።

ግንቦት ሰባት የፖለቲካ እንኪያ ሰላምታን፣ ንትርክንና ውዝግብን አይከተልም። ግንቦት ሰባት ይልቁንም በፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች ዘንድ ያለውን ውዥንብርና ብዥታ ለማጥራት የፍቅርንና የመግባባትን መንገድ ይከተላል። ግንቦት ሰባት ግለስቦችን ሲያናክስና ሲያቧጭቅ እንደውም ጦር ሲያማዝዝ የቆየውን ያለፈውን የግራ ክንፍ የፖለቲካ ባህልና ልምድ አራግፎ በመጣል በውይይትና መቀራረብ ችግሮች እንዲፈቱ ብዙ ይጥራል። የድርጅቱ ዋና ዓላማ ይኸው ሲያባላ የኖረው የግራ እርኩስ መንፈስ ፖለቲካ ከሃገሪቱ ሠማይ ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲጸዳ ነው። እኔ የንጉሡንም የደርጉንም ዘመን ፖለቲካ በወሬ የማውቅ ወጣት ስሆን ዛሬ ከግንቦት ሰባት ብዙ ተምሬአለሁ። ፖለቲካ በተለይም መልካም ፖለቲካ የፍቅር፣ የመግባባትና የመቻቻል ውጤት ለመሆኑ ብዙ ግንዛቤ አግኝቻለሁኝ። ሕዝብ የፍቅር ፖለቲካን ይደግፋል።

በኤርትራ ምድር በረሃ ላይ የሚገኙት ወያኔን በትጥቅ ለመጣል የተሰለፉት ድርጅቶች ከኤርትራ መንግሥት የቁሳቁስ እርዳታ አያገኙም። ምናልባት በድርጅቶቹና በኤርትራ መንግሥት መካከል ሊኖር የሚችለው ስምምነት መሬቱን መጠቀም የሚያስችላቸውን ፍቃድ ማግኘት ሊሆን ይችላል። ይህን በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ያለውን ብዥታ ለማጥራት የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ብዙ ጊዜ ማብራርያ ሰጥተዋል። በእርግጥ ይህ ብዥታ የሚከሰተው ወገኖች ለሃገራቸው ካላቸው ፍቅርና መቆርቆር የተነሳ መሆኑን ግንቦት ሰባት ያምናል ። የፖለቲካ ብዥታ በውይይት፣ በመግባባትና እይታን በማጥራት ይፈታል።

አምባገነኑ ወያኔ ብቻውን ቀርቷል። የሠላሙን መንገድ ረግጦ ጦርነትን የመረጠው ራሱ ወያኔ ነው። ዛሬ እጦርነት ውስጥ ራሱን ሊማግድ የሚፈልገው ወያኔ ማጣፍያው ስላለቀበት፣ መላ ቅጡ ስለጠፋበትና ውሸቶቹ ስላለቁበት ነው። ጦርነት ግን እንዳሰበው አይሆንለትም። ጦርነት እሳት ነው። ሙስናው ወያኔን አበስብሶታል። ወያኔ ለውጊያ ዝግጁ መሆኑ ቀርቶ መራመድ እንኳን ተስኖታል። ወያኔ ማጣፍያው ቢያጥርበት በትዝታ መኖርን መርጦ እተወለደበት ዋሻ ሄዶ አርባ አመቱን አክብሯል። ይህ የተወለደበት ዋሻ ግን ዛሬ መደበቅያው አይሆንም። ዋሻዎቹም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተባብረዋል። ቀድሞ ባለማወቅ የነዚሁ እብሪተኞች መጠለያ የነበሩት ዋሻዎች ዛሬ ተጸጽተዋል።

የኢትዮጵያን አርማ ከፍ አድርገው በተነሱት ነጻ አውጭ ግንባሮችና ወያኔ መሃከል አይቀሬው ግብግብ ቢከሰት ሕዝብ እንደ ቀድሞው እንደማይተባበረው ወያኔ ጠንቅቆ ያውቃል። አዛውንት፣ አዋቂ፣ ሴት፣ ልጅ ሳይል ቃሊቲ፣ ቂሊንጦና፣ ዝዋይ እስር ቤቶች እያሰቃየ፣ ይህ አልበቃ ብሎት ደግሞ በግፍ እየፈጀ፣ በዘር ሸንሽኖ እየበዘበዘ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይተባበረኛል ብሎ ካሰበ የዋህነት ሳይሆን ነፈዝነት ነው። ወያኔን እንኳንስ ሕዝቡ፣ ሥርዓቱን የሚያስጠብቁት የመከላከያ ሠራዊትና ፌደራል ፖሊሶችም ቢሆን አይተባበሩትም። አርበኞች ግንቦት ሰባት የመከላከያ ሠራዊቱንም ፌደራል ፖሊሱንም ይወዳል። ከሕዝባዊ ነጻነት በኋላም እነዚህ የጦር አካላት የሃገሪቱ የጀርባ አጥንት፣ የሕዝብ አጋርና ሰላም አስጠባቂ ይሆናሉ እንጂ በግፍ እንደተበተነው የቀድሞው የሃገር ሠራዊት የትም አይወድቁም።

አርበኞች ግንቦት ሰባት መድኅን ነው። አርበኞች ግንቦት ሰባት ፍቅር፣ መቻቻል፣ ሠላምና የሃገሪቱን አቅጣጫ ወደ መልካም መንገድ መርቶ ሕዝብ ራሱ በመረጣቸው እንደራሴዎቹ እንዲተዳደሩ ለማድረግ ሲል መስዋዕት ለመክፈል የተነሳ የሕዝብ ወገን ነው። አርበኞች ግንቦት ሰባት ከወያኔ ዘረኛው ሥርዓት በቀር አንዳች ጠላቶች የሉትም። አርበኞች ግንቦት ሰባት ሥርዓቱን ለመዋጋት ቆርጦ የተነሳ ድርጅት እንጂ ግለሰቦችን አይጠላም፣ አይማርክም፣ በእስር ቤትና በግዞት አይወረውርም። አርበኞች ግንቦት ሰባት መድህን ነው።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ

ወያኔ/ኢህአዴግ የ20 ሚሊዮን ዶላር ገጸ በረከት ለሄላሪ ክሊንተን ማበርከቱን ተጋለጠ