አማራ ይህ ዓይነቱ ዘግኛኝ ግፍ የሚፈራረቅበት ሌሎች ያጡት ነገር ግን እርሱ ብቻ የጨበጠው ጥቅም ኖሮ አይደለም። አማራ እንደ ሌሎች ወገኖቹ ደሃ ነው። ታድያ ምን አጠፋ -እግዚአብሄርን ማምለኩ፣ ሃገርን፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራውን መውደዱ ነው ወንጀሉ? እንደው ለነገሩ አማራው ብቻ ነው ኢትዮጵያን የሚወደው?ኦሮሞው፣ ጋምቤላው፣ ወላይታው፣ ሲዳማው፣ ጋሞው፣ ቤንሻንጉሉ፣ ጉራጌው፣ ወዘተ፣ ሁሉም ኢትዮጵያን ይውዳል። ለምን ይሆን ታድያ አማራው ለእልቂት የተመረጠው? ምን የተለየ በደል ሰርቶ ነው ሕወሃትና ኦነግ አማራው ሠለባ እንዲሆን የፈረዱት? ቅኝ ገዥዎች የተሸነፉት በመላው ኢትዮጵያዊ ትብብር ነው። አማራው ብቻውን አድዋ አልዘመተም። ግን ለምን ይሆን አማራው ላይ ብቻ እልቂት፣ ግድያ፣ እገታ፣ ማምከን፣ ንብረት ማቃጠል፣ ወዘተ፣ የተፈረደው? በእርግጥ አማራው ላይ እልቂት እንዲፈጸም ሠይጣናዊ ሃሳቡን ያረቀቀው ወያኔ "ዘር ከዘር አፋጅቴ ኢትዮጵያን ለሺህ ዓመት በማን አለብኝነት እገዛለሁ" ከሚል አላዋቂነት የተነሳ ነው። ወያኔ ይህን ድንቁርና የወረሰው ከቅኝ ገዥዎች ነው። ይህን አላዋቂነት ጽንፈኞችና አማራ-ጠል ምሁራን ተጋሩት። ይህን አላዋቂነት ሃገር እንድትፈርስ የሚፈልጉ ሁሉ ከአድማስ አድማስ አናፈሱት። በዘር እልቂት ሽፋን ሚኒልክ ቤተ መንግሥት መግባት የሚፈልጉ ሁሉ ዘረኝነትን በወጣቶች ዓዕምሮ ውስጥ እንዲያድር ብዙ ደከሙ።