Friday, July 8, 2016

ኤስፍና ESFNA እና AESA One ታሪካዊ ግብግብ

ኤስፍና ESFNA እና AESA One ታሪካዊ ግብግብ
ከ ሚኪያስ ግዛው
በሁለቱም ሜዳዎች ላይ ባንዲራዎች ይውለበለባሉ። በሁለቱም ሜዳዎች ላይ ኳሶች ይነጥራሉ። በሁለቱም ሜዳዎች ላይ ድምጻውያን ይዘፍናሉ። በሁለቱም ሜዳዎች ላይ ማልያ የለበሱ ሰዎች ይታያሉ። ሁለቱም ሜዳዎች ግን ልዩነቶች አሏቸው። አንደኛውን ሜዳ ደማቅ ቀለማማ የብርሃን ፍንጣቂ ከቦታል። አንደኛው ሜዳ ላይ ደግሞ ጨለማ ሠፍኗል። በሁለቱም ሜዳ ላይ ተመልካቾች አሉ። ባንደኛው ሜዳ ላይ ጢቅ ብለው የሞላው ሕዝብ ብርሃኑን መልሶ ያንጸባርቃል። በሌላኛው ሜዳ ላይ ደግሞ የተቸረከሙት ጥቂት ሰዎች በዘረኝነቱን ጨለማ ተውጠዋል። በሁለቱም ሜዳዎች ላይ ሰዎች ይታያሉ። ምነው ታድያ አንደኛው ሜዳ ላይ ያሉት ሰዎች እንደ ኃጢዓቱ ምርከኞች ኩርምት አሉ?
እነዚህን ወገኖች ነጻ ማውጣት አለብን። እነዚህን ወገኖች ከጨለማው አውጥተን ወደ ብርሃኑ ለማምጣት ማስተማር፣ መምከር አለብን። ታድያ እንዴት ይሆናል! እኔም ጭንቅ አለኝ!
አዎ - ይህን ሳሰላስል ድንገት ቶሮንቶ (Toronto) ላይ እምዬ ሚኒልክ ምስላቸው ብቅ አለ። በግርማ ሞገሥ የተከበቡት፣ የዋህና ደጉ ንጉሣችን እምዬ ሚኒልክ በፈረሳቸው ዳኛው ላይ ተቀምጠው ድንገት ብቅ ሲሉ ታየኝ። በስታድዮሙ ውስጥ ሌላ ብርሃን ተንጸባረቀ። በምድረ ዓለም ገድላቸው ተነግሮ ያላበቃው የነጻነቱ አባት እምዬ ሚኒልክ "ይህችን ባንዲራ ጠብቋት፣ ብዙዎች ለዚህች ባንዲራ ሲሉ ተሰውተዋል" አሉ በዚያ የዋህ ድምጻቸው። ይህ ድምጽ የስታድዮሙን ግድግዳና የአካባቢውን ሕንጻ በርቅሶ፣ በአየር እየተንሳፈፈ አኤስዋኖች (AESA One)ኩርምት ብለው የቀመጡበት አሌክሳንዴርያ ቨርጂንያ (Alexandria, Virginia)ጨለማው ዋሻ ደረሰ። ድምጹ እንደ ሳይክሎኑ( cyclone) ነፋስ ገረፋቸው፣ ገፈታተራቸው። አዎ እነዚህ በነዋይ ምርኮ ታግደው፣ ቀለብ ተሰፍሮላቸው በጨለማው ውስጥ ዘረኝነቱን ለማድመቅ የተቀመጡ የዋሆች በቶሎ ነጻ ይወጣሉ። የእምዬ ሚኒልክ ድምጽ እንኳንስ ለወገን ለባዕድም ማዕዛ አለው። ነዋይና ስጋቸው በእሳት እንደተበየደ ብረቶች ከተዋሃደው ጥቂቶቹ ቱባ የዘረኝነቱ አዳማቂዎች በቀር ሌሎቹ ቶሎ ነጻ ይወጣሉ።
አሁንም ጭንቅ ይለኛል። በደጉ ዘመን ተንቀባረው ይኖሩ የነበሩት፣ በዘመኑ አጠራር "የዲታ ልጆች" የሚባሉት ግለሰቦች ለምን ለጨለማው ሥራ ተባባሪዎች እንደሆኑ ማወቅ አልቻልኩም። ወያኔ በአብዛናው በሥሩ ያሰለፋቸው ምርከኖች ትላንት "በአማራው ስትጨኮን የነበርህ ነህ" የተባሉ ጥቂት ተላላ ድንባዣሞች ሆኖ ሳለ - ያኔ ተንቀባረው ያደጉ ግለሰቦች ለምን ምርከኞች እንደሆኑ ማሰቡ ያዳግታል። ገንዘቡ አታሏቸው ነው እንዳይባል እኛ የሳር ፍራሽ ሲበዛብን እነሱ ተዝቆ የማያልቅ ገንዘብ ተንተርሰው ያደጉ ቅምጥሉች ናቸው። ሥልጣን ፈልገው ነው እንዳይባል ደግሞ ሥልጣን የያዙ አልያም የባለሥልጣኖች መጋቢ አሽከር ተከታይ ሆኑ እንጂ የነእገሌን ያህል እንኳን ክብር አልተሰጣቸውም። ምንድነው እነዚህን ግለሰቦች ለዘረኝነቱ ጨለማ ተገዥ ያደረጋቸው። ንዋይ፤ ሥልጣን፤ የተወረሰባቸውን ቦታና ቤት ለማስመለስ ወይንስ የዓዕምሮ መላሸቅ? ያ ሁሉ ትምህርት ምነው ላሸቀ እነዚህን ወገኖችም እንዴት አድርገን ነጻ እንደምናወጣ አላውቅም። አንድም ሰው ቢሆን በዘረኝነቱ ጨለማ በምርኮ እንዲሰቃይ አንፈልግም። ለነዚህም ወገኖች መልካም ልብ እንስጣቸው። በጓደኞቻቸው እናስመክራቸው።
ኤስዋን AESA One ሰዎች ከዚህ ውርደት ልትማሩ ይገባል። ሕዝብ በማይደግፈው ነገር ውስጥ ከመሳተፍ ልትቆጠቡ ይገባል። ዲሞክራሲ ማለት የአብዛኛ ሕዝብ የበላይነት ማለት ነው። ይህ ደግሞ ሳይገባችሁ አይቀርም። ቁጥሩን መገመት ትችላላችሁ። ዘረኝነት አናሳ ነው። ዘረኝነት ኢትዮጵያዊነት አይደለም። ኃያላኑ ሃገሮች ለጊዜዊው ጥቅማቸው ሲሉ ዘረኝነቱን ቢያሞካሹትም እንኳን እናንተ የእምዬ ሚኒልክ ልጆች ልትታለሉ አይገባም። ነገ እንትፍ ብለው ከሚጥሉት ዘረኝነት ጋር ብትወግኑ ነገ የምታዝኑት እናንተው ናችሁ። ለልጅ ልጆቻችሁ ነጻነት ከወዲሁ አስቡበት። የባንዳ ልጅ፤ የምንትስ ልጅ ለምንስ ይባሉ።
ኤስፍና ESFNA እና AESA One የዲያስፖራው ኢትዮጵያው ሌላኛው የግብግብ አውድማዎች ናቸው። ግብግቡ ሰው ከሰው ጋር አይደለም። ግብግቡ ኢትዮጵያዊነት ከዘረኝነት ጋር ነው። ከእግዚአብሄር መንፈስ ጋር አታመሳስሉት እንጂ ሁለቱም መንፈሶች ናቸው። አንዱ ኢትዮጵያዊ መንፈስ፣ አንዱ የዘረኝነቱ የጣር መንፈስ። የኋላ ኋላ የዘረንነቱ የጣር መንፈስ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ መሸነፉ አይቀርም። ይህ እውን እስኪሆን ለጥቂት ጊዜ ግብግቡ ይቀጥላል።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር፣ ባዲራችን ለዘላለም ትውለብለብ።
ክብር ለአጼ ቴዎድሮስ፣ ክብር ለአጼ ዮሃንስ፣ ክብር ለእምዬ ሚኒልክ

No comments:

Post a Comment