Monday, February 15, 2021

 ኢትዮጵያ ምንም አትሆን፣ ግን እስከመቼ እንዲህ በስቃይአምላኬ?

ሚክያስ

ኢትዮጵያ ትላልቅ አደጋዎችን ተቋቁማ ነው ኅልውናዋን የምታስቀጥለው። በፋሽስት ኢጣልያ ወረራ ወቅት ንጉሡ ሀገር ጥለው ቢሰደዱም እነ አበበ አረጋይ፣ ኃይለማርያም ማሞ የመሳሰሉ ጀግኖች መንግሥትዋ የተበተነ ኢትዮጵያን ታደጉ። ኢጣልያ ባንድ በኩል ከጀርመን ጋር ያደረገችው መተባበር ዓለም አቀፍ ጫና ሲያሳድርባት በሌላ በኩል ደግሞ አርበኛች ያሳረፉባትን ዱላ መቋቁም ተስኗት አዲስ አበባን ለቃ ፈረጠጠች። ደርግ ሥልጣን በያዘ ማግስት ዘመናዊ ሶቭየት ሕብረት ሠራሽ ብረት ለበስ የጦር መሳርያ እስከአፍንጫዋ የታተቀችዋ ሶማልያ ድንገት ወረራ ስታደርግም ኢትዮጵያ ዝግጁ አልነበረችም። ንጉሡ ከአሜሪካ የሸመቱትን መሳርያ ማስረከብ ያልፈለገው የአሜሪካው ፕሬዚዴንት የካርተር አስተዳደር ኢትዮጵያን እጅግ ነበር የጎዳት። ይሁንና ግን ባጭር ጊዜ ውስጥ ሠልጥኖ ወደ ግምባር የገባው ሚሊሽያ ለወራት በጀግንነት ሲከላከል ለቆየው የኢትዮጵያ አየር ኃይልና የጦር ሠራዊት ብርቱ አጋዥ በመሆን ሶማልያ በቁጥጥሯ ስር አድርጋ የነበሩትን መሬቶች ለቃ ወደ ሞቃዲሾ እንድትፈረጥጥ አደረጋት። ኢትዮጵያ ሌላ መከራም ወደቀባት። ሕወሃት የተባለ ከኢጣልያም ሶማልያም የባሰ ነጻነቷን የሚለበልብ እርኩስ ዘረኛ ኃይል ከራሷ ጉያ ውስጥ ወጣ።

የህወሃት የዘር ፖለቲካ ኢትዮጵያን ወደብ አልባ በማድረግ፣ ድህነትንና ስደትን በማባባስ ብቻ አላበቃም፤ አማራውን በማስፈጀት ጭምር እንጂ። ህወሃት አራት ኪሎ እንደገባች የዘር ፖለቲካውን በአማራው አንገት ላይ እንደ ዘንዶ ጠመጠመች።"በዘሩ እየተመካ ብሄረሰቦችን ሲጨቁን የነበረው አማራ እንጂ ትግሬ አይደለም፣ ትግሬን ትታችሁ አማራውን ፍጁየሚል የዘር መድሎ (apartheid)ህግ የቀረጸችው ህወሃት እልቂቱን የበደኖውና አርባጉጉው ተራራ አምባሳደር አድርጋ በላከችው አቶ ታምራት ላይኔ በኩል ተፈጻሚ አደረገች። የዘር ማጽዳቱ (ethnic cleansingሂደት በቡርቃ ዝምታ ትርክት ጎልብቶ የመኖር ዋስትና በተነፈገው ደሃው አማራ ላይ ተከታተለ። ለሰላሳ ዓመታት መዋቅራዊ ድጋፍ ተችሮት በበደኖና አርባጉጉ የተጀመረው አማራውን የመፍጀት (genocide) እቅድ የተፈናቃዮችና የሟቾች ቁጥር በማስመዝገብ ብቻ እየታለፈ ነው። አማራው ላይ የሚደረገው የዘር ማጽዳትና የዘር ፍጅት በግጥምና በጽሁፍ ብዛት፣ በሠላማዊ ሠልፍና ስብሰባ ውግዘት፣ በሃዘን መግለጫዎችና ማሳሰብያዎች እሮሮ፣ በፍትሃትና ነፍስ ይማር ጸሎት ሊቆም አልቻሉም። ማዕከላዊውን ኃይል ማጠናከር ያልቻሉት ዶክተር አብይ ከመጡ በኋላም አማራው እየታረደ ነው።

ዶክተር አብይ የቀድሞው ህወሃት የዝርፊያ ሥርዓት ተጠቃሚዎቹን ዓዕምሮ ሳያጸዱ ደምረው ያቋቋሙት ብልጽግና ሁለት ተጻራሪ ፍላጎቶች ያሏቸውን ቡድኖች አንድ ላይ የሰበሰበ ድርጅት ነው። ይህ ውስጣዊው ችግር የዶክተር አብይን የመምራት አቅም ውሱን አደረገው። ኦነግ ሸኔ -እምዕራብ ወለጋ ላይ በከፈተው ጦርነት ሳብያ በኢትዮጵያ ውስጥ የተረጋጋ መንግሥት እንዳይኖር ሆነ። ዶክተር አብይ በምዕራብ ኢትዮጵያ ሃገርን ያስተዳድራሉ ማለት አይቻልም። የዶክተር አብይ መንግሥት መከላከያ ኃይል ፊት ለፊት ካገኘው ኦነግ ሸኔ ጋር ሲፋለም – የኦነግ ደጋፊ የሆኑት ብልጽግና ውስጥ ያሉ ረድፈኞች እጫካ ካለው ኦነግ-ሸኔ ጋር ይደራደራሉ። መከላከያው አባ ቶርቤን ሲከላከል እነዚሁ ረድፈኞች በሌላ ስውር መንገድ አማራውን ያስጠቃሉ። እርሳቸው ዶክተር አብይ ጉያ ሥር ተሸሽገው ያሉት መሠሪዎች ኢትዮጵያን መንግሥት አልባ አደረጋት።

ቁጥር ሥፍር የሌላቸው የኦሮሞ ምሁራን በብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ ስለሚረኩ ህወሃትን እንደ ባለውለታ አማራን እንደ ጠላት ይመለከታሉ። የኦሮሞ ፖለቲከኞች "አሃዳዊበሚለው ቅርጽ እየባነኑ ነው። የብሄር ብሄረሰብ ቀለም ቀብታ ክልልነትን ከአንቀጽ 39 ጋር "እንኩያለችው ህወሃት ከመቶ ዓመት በላይ ለመግዛት፣ ከፍተኛ ኃብት እውጭ ለማስቀመት፣ ጥሬ ሃብት ወደ ትግራይ ለማሸሽ፣ ወዘተ፣ ነበር እንጂ ፌደራሊዝም ተስማምቷት አልነበረም። ህወሃት ከንጉሥ ኃይለሥላሴም ይልቅ ጨቋኝ አሃዳዊ ነበረች። ይህ መሰሉን ህወሃት የተጠቀመችበትን የተበላ እቁብ ፖለቲካ እንደገና አድሶ ሌላ ምዝበራና ስርቆት እፈጽማለሁ የሚለው ተረኛ፣ ይህ ተላላ ፖለቲከኛ – ለሕዝብ ተቆርቋሪ መንግሥት የሆነ መንግሥት እንዳይኖር በማድረግ አማራን አስፈጀ። ብልጽግና ውስጥ ያሉት ተጻራሪዎች የጀርባ ላይ እባጭ የሆኑባቸው ዶክተር አብይ እነሱን ለማርገብ የተጠቀሙት ሌላናው ዘዴ ኦሮሙማን ማጠናከር ሆነ። እነሆ በመሬት ዝርፊያና ሥልጣንን በማጠናከር ላይ ብቻ የሚያተኩረው የኦሮሙማ ፖሊሲ ኢትዮጵያን ክብሯን ለማስጠበቅም ሆና አማራን ከዘር ጥቃት ለመጠበቅ የሚያስችል አቅም የለውም።

ዶክተር አብይ ህግና ሥርዓት ማስከበረ ካልቻሉባቸው አካባቢዎች አንዱ የደቡብ ኢትዮጵያ ምድር ነው። "ክልል ልሁንያለው የሲዳማ መሬት ክልል እስኪሆን ድረስ በዘር ዱላው አርባ ተገርፏል። አሁንም "ክልል ካሎሆንን ሞተን እንገኛለን"የሚሉት የደቡብ መሬቶች እራሳቸው ዶክተር አብይ በላኩት በአባ ዱላ በትር ሳይገረፉ እንዲሁ ክልል አይሆኑም። የዘር ፖለቲካው የወለደው ክልል የተባለው እንግዴ ልጅ – መልክዓ-ምድራዊም ሆነ አስተዳደራዊም ቅርጽ የማይበጅለት የደመ ነፍሱ ህወሃት የጋኔን ምች ነው። ክልል የዘር ፖለቲካው መሪ የተራራው ጀርባ ዓጽመ ርስት ነው። አንዱ የነቃ ጮሌ "ክልል እንሁንብሎ ያሳምጻል፣ ብዙዎች ሞተው፣ ተገርፈው መሬቱ ክልል ሲሆን፣ ጮሌው ከዱላ የተረፉትን ወገኖቹን በፍርሃት ቆፈን አስሮ ይግጣቸዋል። የዘር ፖለቲካ ትወና የተካነች፣ ውሸታሞች የሚያበለጽጓት፣ እርጉም ባህል መሆኗ ፍንትው ብሎ የታየው አዋሳ ከተማ ውስጥ አብሮ የኖረው ወንድማማቹ የወላይታና ሲዳማ ሕዝብ አንገት ላንገት ተያይዞ ሲቀነጣጠስ ነው።

የዘር ፖለቲካ እረፍት የላትም። በጉራ ፈርዳ፣ ቤንች ማጂ ምድር የሚንቀለቀለው የዘር ፖለቲካ ደራሽ የሌለውን አማራ ወገኔን ቁም ስቅሉን አብልታለች። ቤንሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ምድርን በቀርክሃ ዱላ ስትገርፍ የቆየችው የዘር ፖለቲካ ዞር ብላ ደግሞ ፍርጃ ያልተለየውን አማራን በሾለ ቀስት ቀሰፈችው። ግፍ ክፉ ነች፣ ነገ ተመልሳ የቤንሻንጉል ጉሙዝ የዘር ግድያ መሃንዲሶች ላይ መከራ ታዘንባለች።

ለኢጣልያ ያደሩ ባንዶች የወለዷቸው ልጆች ያፏፉት የዘር ፖለቲካ ቀማኖችን እንጂ ብቁ አስተዳዳሪዎችን አላበቀለም። የዘር ፖለቲካ ለተላላኪው ጫት መቃምያ፣ ለአስመሳዩ ጮማ መቁረጭያ፣ ለጮሌው ንዋይ መሰብሰብያና የምዕራብ ሃገሩ መኖርያ ፈቃድ ማግኛ ነች። ሰው ሳይደክም ላገኘው ገንዘብ አይሳሳም። ሕወሃት ነፍሷን አይማረውና ብልግናን አስፋታ ነው ወደ መቃብር የወረደችው። ዛሬም አንድ ባለሥልጣን ራስ ምታት ቢይዘው አስፕሪን ለመዋጥ አውሮፓና አሜሪካ ለመሄድ ይዳዳል። እንግዲህ አስቡት፣ ደሃው በዋጋ ግሽበት እያለቀሰ፣ ወጣቱ ሥራ ፍለጋ እየደከመ ይህ ሁሉ የውጭ ምንዛሬ ሲባክን ሜድያው እንደዘበት "እገሌ ሊታከሙ አሜሪካ ገቡ"ብሎ ያወራል።

ባለሥልጣናቱ በሶስት ምክንያቶች ወደ ውጭ እየሄዱ የውጭ ምንዛሬ ያባክናሉ፣ አራተኛው ደግሞ ጉደኛ ነው። አንደኛው ምክንያት መዝናናት ነው። "የደላው ሙቅ ያኝካልእንዲሉ ለመዝናናት ውጭ ይሄዳሉ። በንጉሡና በደርግ ዘመን ሶደሬ ወይንም ላንጋኖ መሄድ እንደማለት ነው። ሁለተኛው ምክንያት ስጋት ነው። ልዩነት ሲከሰት ስጋት የሚያድርበት ባለሥልጣን በህክምና አስታኮ ዞር ብሎ ሁኔታውን የሚከታተለው እምዕራቡ ሃገር ባለው ዩ ትዩብና ፌስ ቡክ ነው። ሶስተኛው ምክንያት ጸጸትና ፍርሃት ናቸው። ዘረኞች የግፍ ሥራቸው ሁልጊዜ ያባንናቸዋል። እነዚህ ባለሥልጣናት ኦዲት ከማይደረገው የሃገሪቱ ኃብትና የመሬት ወረራ ድርሻቸውን ሞጭልፈው ቤተሰቦቻቸውን አስቀድመው ልከዋል። ኮሽ ሲል በስብሰባ ስም ዶላር አፍሰው እግሬ አውጭኝ ይላሉ። ችግሩ ከተባባሰ እዛው ይቀራሉ። አራተኛው የጉድ ነው። ለፍርድ መቅረብ የሚገባቸው ወንጀለኞች በሞቀ ሽኝት አምባሳደር ተደርገው ይላካሉ። ወገኖቼ እንግዲህ ፍረዱበንጉሡና በደርግ ዘመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጥራትንና የአምባሳደር አሿሿም መስፈርትን አጢኑ። እንደው ለመሆኑ አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ "Compare and contrast Intellectual and Moral integrity during the reign of Emperor Hailesselasie with that of both EPRDF 1 and EPRDF 2» ብሎ ቢጽፍ አርዕስቱ ብቻ A+አያሰጠውም።

መጣጥፉን እንዲህ ብሎ ቢጀምርስ፣ "ሃገሬ ኢትዮጵያ የጉድ ሃገር ከሆነች ሠነበተች። በዓለም ባንክ ብድር የሚሰሩት ፋብሪካና ኢንዱስትሪዎች ከሁለት አቅጣጫ ሲቦተለኩላቸው ቆይተዋል። አንዱ ከአበዳሪዎቹ ሲሆን ሌላው ከተበዳሪው የሃገራችን መንግሥት ነው። ፕሮፕጋንዳዎቹ ግን አቅጣጫ ማስቀየሻ እንጂ የሃገር ኃብት ሲሆኑ አልያታየም። አበዳሪ ሃገራትና ሙሰኛ መሪዎች በምክክር ስለ "ድርብ አሃዝ እድገትሰምና ወርቅ ሲቋጥሩ የሸቀጦች ዋጋ ይንራል፣ ሥራ አጥነት ይስፋፋል፣ ድህነት ይባባሳል። ባለሥልጣናት በዘረፉት ገንዘብ እውጭ ላስቀመጧቸው ልጆቻቸው ወጪ ሲሸፍኑ ብድሩ ተመልሶ አበዳሪው እጅ ይገባል፣ እዳውን ኢትዮጵያ ትከፍላለች። ብድርና ዘረኝነት ተጣምረው ለኢትዮጵያ ሃገሬ የቆላ ቁስል ከሆኑ ሶስት አስርት ዓመታት ሆናቸው። ይህ የቆላ ቁስል እንዲሽር ደጋጎች የወጠኑት ኦሮ-ማራ በኦሮሙማ ክፉ ሃሳብ ተዋጠ። ኦሮሙማ የዘረኝነቱ ፖለቲካ ክፍል ሁለት ነች"

ክፉ ለራሱ ደግ ለራሱ ነው። ግፍ ውላ አድራ አርሞ ኮትኩቶ ያሳደጋትን እንደምትበላ በገሃድ የታየው አቶ ስብሃት፣ ባለቤታቸውና እህታቸው ወታደሮቹ ከገደል ተሸክመው ሲያወጣቸው ነው። የዘር ፖለቲካ ልጆቿን ተራ በተራ ቅርጥፍ አድርጋ በልታቸዋለች። የዘር ፖለቲካ ተመራማሪ፣ አንባቢ የተባለውን መለስ ዜናዊና ቡራኬ ሰጭዋን ጳጳስ ሳይቀር በሾሉ ጥርሶቿ አኝካ ውጣ የተረፉትን አንገላታና አባዝና ጊዜው ሲደርስ እስከነ ጓንታቸው ሠለቀጠቻቸው። እንደ ጎርፍ በፈሰሰው ደም የተገዛ ምድራዊ ቅንጦትና ሃገር ማቅ አልብሶ እውጭ ገንዘብ ማሸሽ መጨረሻው ዛሬ ያየነው ነው። ሕወሃቶች ተዋርደው እንዲህ መቀመቅ ሲወርድ እያዩ አሁንም ዘረፋና መሬት ወረራ የሚያስቡ ኦሮሙማዎች በእውነት ቂሎች ናቸው ። ትልቁ ባለሥልጣን፣ የቀድሞው የትግራይ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ ለማኝ ሆነው ራሳቸውን ክደው ሃሰን እብራሂም ነኝ እያሉ ሲዋሹ የዘር ፖለቲካ በእርግጥም ላሳዳጊዋም እንደማትሳሳ ፍንትው ብሎ ያሳያል። ወገኖቼ ይህን ሁሉ እያየን ዓለም ከንቱ መሆኗን ካልተረዳን አሁንም ሞኞች ነን። ስብሃት ነጋ "እኔን ያየህ ተቀጣእያሉ ሳለ ዛሬም በዘረፋና በቅሚያ ለማደግ መጓጓቱስ የት ያደርሳል?ወገኖቼ አሁንስ ይመራል። ሥልጣንና የመሬት ወረራ የአንድ ስንቲም ሁለት ግልባጭ በሆኑባት ኢትዮጵያ እንደምን አድርጎ ፍትህ ማስፈን፣ አማራውን ማዳን እንደሚቻል ማሰቡ እጅግ ይከብዳል። ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት ወራ እስከምትይዝ፣ እንዲህም ተዋርደን አናውቅም። በእርግጥ ኢትዮጵያ ምንም አትሆን፣ ግን እስከመቼ እንዲህ በስቃይአምላኬ?

ፈጣሪ እባክህ አማራውን ታደገው፣ ኢትዮጵያን ስቃዩን አንሳላትአሜን።


Tuesday, February 2, 2021

#Abiy stop killing Amhara

 የአማራው ለብቻው መደራጀት ኢትዮጵያዊነትን ያዳክማል?


አንድ ወቅት ላይ አፍቃሪ ወያኔ የሆነው የኢትዮጵያ ፊርስት ድረገጽ አዘጋጅ ቤን የተባለው ጋዜጠኛ አቶ መለስንና አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ቃለመጠይቅ አቅርቦላቸው ነበር። አቶ መለስን እንዲህ ሲል ጠየቃቸው።(ቃለ መጠይቁን ስለረሳሁት ሃሳቡን እንጂ ቃል በቃል ላስቀምጠው አልችልም)። "እንደው ኦሮም ኦሮሞ ሲባል ይለጠጥና ኢትዮጵያዊነትን አያዳክምም?" እርሳቸው ሲመልሱም "አያዳክምም ኦሮሞው በኦሮሞነቱ ማንነቱ ሲከበርለትና እውቅና ሲሰጠው እንደውም ኢትዮጵያዊነት ያጠናክራልአሉ። በሌላ ጊዜ ደግሞ አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ጠየቃቸው። "እንደው ይህ በዘ በዘሩ መደራጀት ኢትዮጵያዊነትን አያላላም፣ አያፈርስም?" እሳቸውም እንደ አለቃቸው ሲመልሱ "አያዳክምም ለምሳሌ እኔ ሲዳማ ነኝ ሲዳማነቴ ሲታወቅልኝና ማንነቴ ሲከበርልኝ ኢትዮጵያን እወዳታለሁ። ስለሆነም ኢትዮጵያዊነት ይጠናከራል"። ሁለቱም መልሳቸው ላይ ማንነት (identity) ምትለዋን ጽንሰ ሃሳብ አንስተዋል። ማንነታቸውን ያወላገደባቸው አማራ ነው ወይንም ሁሉንም ገዥዎች አማሮች ናቸው ለማለት ነው። ይህ የተሳሰተ ፍልስፍና፣ ወደ ስልጣን ላይ ለመውጣት የተፈበረከ ይህ እኩይ ፍልስፍና ነው አማራውን ያስጠቃው። ወያኔና ሻዕቢያ የሁሉም ዘር ጠላት አማራ ነው ሲሉ ለልጆቻቸው እያስተማሩ በምስኪኑ አማራ ላይ የግፍ ጣታቸውን ቀሰሩበት። አማራው የተሳለቀበትና ማንም እየተነሳ የሚያንቋሽሸው በዚህ ፍልስፍና፣ እዛው ደደቢት ውስጥ በተቀመረው የተሳሳተ ርኩስ ንድፈሃሳብ ነው።