ሕወሃት አዲስ አበባ ከከተመበት ቀን ጀምሮ የታወጀው አማራውን ከምድረ ገጽ የማጥፋት ዶክትሪን - ዶክተር አብይ ሥልጣን ላይ ሆነውም አልተገታም። ዛሬ ላይ ገሃድ የሆነው የዘር ፍጅትና አስቃቂ ግድያዎች የሕወሃት የዘር ፍጅት ምዕራፍ ቅጥያ ነው። የዛሬ ሠላሳ ዓመት ገደማ ጠባቂና ተከላካይ የሌለው ምስኪኑ አማራ በወያኔው ሹም ትዕዛዝ አርባጉጉና በደኖ ላይ ከገደል ተወርውሯል። ኦርቶዶክሱና አማራው ላይ ያነጣጠረው ይህ ዘርን የማጽዳት አረመናዊ ጭፍጨፋ ከቡራዩ እስከ አዲስ አበባ፣ ከአርሲ እስከ አዳማ፣ ከባሌ እስከ ሐረርጌ፣ ከሻሸመኔ እስከ አርሲ ነገሌ፣ ወዘተ፣ ተካሂዷል። አማራውና ኦርቶዶክስ ክርስትያኑ ላይ የደረሰው የዘር ፍጅት ናዚ ጀርመን እስራኤሎች ላይ ካደረገው እልቂት በዓይነት ይለያል።፣
አማራ ይህ ዓይነቱ ዘግኛኝ ግፍ የሚፈራረቅበት ሌሎች ያጡት ነገር ግን እርሱ ብቻ የጨበጠው ጥቅም ኖሮ አይደለም። አማራ እንደ ሌሎች ወገኖቹ ደሃ ነው። ታድያ ምን አጠፋ -እግዚአብሄርን ማምለኩ፣ ሃገርን፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራውን መውደዱ ነው ወንጀሉ? እንደው ለነገሩ አማራው ብቻ ነው ኢትዮጵያን የሚወደው?ኦሮሞው፣ ጋምቤላው፣ ወላይታው፣ ሲዳማው፣ ጋሞው፣ ቤንሻንጉሉ፣ ጉራጌው፣ ወዘተ፣ ሁሉም ኢትዮጵያን ይውዳል። ለምን ይሆን ታድያ አማራው ለእልቂት የተመረጠው? ምን የተለየ በደል ሰርቶ ነው ሕወሃትና ኦነግ አማራው ሠለባ እንዲሆን የፈረዱት? ቅኝ ገዥዎች የተሸነፉት በመላው ኢትዮጵያዊ ትብብር ነው። አማራው ብቻውን አድዋ አልዘመተም። ግን ለምን ይሆን አማራው ላይ ብቻ እልቂት፣ ግድያ፣ እገታ፣ ማምከን፣ ንብረት ማቃጠል፣ ወዘተ፣ የተፈረደው? በእርግጥ አማራው ላይ እልቂት እንዲፈጸም ሠይጣናዊ ሃሳቡን ያረቀቀው ወያኔ "ዘር ከዘር አፋጅቴ ኢትዮጵያን ለሺህ ዓመት በማን አለብኝነት እገዛለሁ" ከሚል አላዋቂነት የተነሳ ነው። ወያኔ ይህን ድንቁርና የወረሰው ከቅኝ ገዥዎች ነው። ይህን አላዋቂነት ጽንፈኞችና አማራ-ጠል ምሁራን ተጋሩት። ይህን አላዋቂነት ሃገር እንድትፈርስ የሚፈልጉ ሁሉ ከአድማስ አድማስ አናፈሱት። በዘር እልቂት ሽፋን ሚኒልክ ቤተ መንግሥት መግባት የሚፈልጉ ሁሉ ዘረኝነትን በወጣቶች ዓዕምሮ ውስጥ እንዲያድር ብዙ ደከሙ።
ሃገር ጠሎች - አማርኛን፣ የቅኝ ግዛት ሽንፈት ምልክት የሆነውን የሚኒልክን ሃውልት እንደጦር ይፈራሉ። አማርኛ እኮ የአማራ ብቻ ቋንቋ አይደለም። የሚኒልክ ሃውልት እኮ የኢትዮጵያ ብቻ መኩርያ አይደለም። መላው አፍሪካና በቅኝ ግዛት የማቀቁ ሃገሮች ሁሉ የሚኒልክ ሃውልትን ይወዳሉ። በብዙዎች የአፍሪካ ሃገራት እኮ በሚኒልክ ስም አደባባይ፣ መንገድ፣ አዳራሽ፣ ትምህርት ቤት፣ ወዘተ፣ ተሰይሟል። "የሚኒልክ ሃውልት ይፍረስ" የሚለውን የቅኝ ግዛት ሃሳብ በሞኝ ምሁራን ዓዕምሮ ውስጥ አስቀምጠው ሲዘርፉ የነበሩ ወያኔዎች የማታ ማታ የት ደረሱ? ዛሬ በሕይወት ያሉት ወያኔዎች ወደ ቀልባቸው ተመልሰው በወገናቸው አምሃራው ላይ የደረሰው እልቂት ይከነክናቸው ይሆን? እግዚአብሄር ይወቀው። አቶ ስብሃት "አማራና ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን አከርካሬአቸው ተሰብሯል፣ ከዚህ በኋላ አያንሰራሩም" ሲል የተናገረው አረፍተ ትዕቢት - "ነፍጠኞች የሠበሩን ቦታ ላይ ቆመን ነፍጠኞችን ሰብረናል" ወደሚለው አረፍተ-ከንቱ ማደጉ ያሳዝናል እንጂ የሳይንስ እድገት ማሳያ ጥበብ አይሆንም። ወያኔ ያበላሸውን ሥርዓት ዳግም ለማበጀት ግብረገብ ማስተማሩ እንጂ ማሳሳቱ ምን ይበጃል? ለዓመታት የተደከመባቸውን በጥቂት ደቂቃዎች በእሳት አጋይቶ ማውደም ሃይፐር ሶኒክ ጄት እንደ መሥራት የሚኮራቸውን ግፈኞች መክሮ ገስጾ መመለሱ እንጂ ማመጻደቁ ምን ይበጃል?እግዚአብሄር እኮ ሁሉን ያያል። አምላክ እኮ የምስኪኖች ዋይታ ይሰማል።
ባለፈው “ተከብቤአለሁ” ሳብያ የሞቱ ዜጎች ሃዘን ሳይወጣልን - በሰሞኑ ጥቃት ሻሸመኔ እንደ ሶርያዋ አሌፖ ስትጋይ፣ ምስኪኖች እጅና እግራቸው ተቆራርጦ አቅመ ደካሞች ደግሞ በገጀራና ጦር ተሸቅሽቀው ተገድለዋል፣ አንድ ባለሉካንዳ ተገድሎ በሥጋ መስቀያ ሜንጫ ላይ ተንጠልጥሏል። ጥቃቱ ጅማንም መቷል። በሰሞኑ ፍጅት ባጠቃላይ ከ230ሰዎች በላይ ተገድለው ሌሎች 200 ያህል ሰዎች ቁስለኛና አካለ ጎዶሎ ሲሆኑ 250 መኪኖች ተሠባብረው፣ 20 ያህል ተቃጥለዋል። አረመኔዎች 35 ፎቆች እንዲሁም ከሺህ በላይ መኖርያ ቤቶች አቃጥለው ጨፍረዋል። በቦስንያ ጭፍጨፋ ሰው ተዘቅዝቆ አልተሰቀለም። አርመኖች ላይ በደል ሲፈጸም የሴት ልጆች ጡት አልተቆረጠም፣ ሰው ተዘቅዝቆ አልተሰቀለም። የአርሲ ነገሌውና የሻሸመኔው ውድመት ከሩዋንዳው እልቂት ጋር ሲነጻጸር እንኳን በዘግናኝነቱ ላቅ ይላል። የሰው ልጅ በፍቅርና በመተሳሰብ በሚኖሩባት የምድር ገነት ተብላ በምትወደሰው ኢትዮጵያ - ኦነግ ሸኔ በአይዞህ ባዮቹ እየታገዘ ማንንም ሳይፈራ ጥቃት ፈጽሟል። እስላም ክርስትያን የሞሉባት ኢትዮጵያ ውስጥ ዘግናኝ እልቂት መፈጸሙ እጅግ ያስለቅሳል።
መንግሥት የዘር ፍጅት ሲፈጸም፣ ጥብቅ ቁጥጥር ባለማድረጉ ተጠያቂ ነው። ግፈኞች - ደሞዝ የሚከፈላቸው ባለሥልጣኖችና ሥርዓት አስጠባቂዎች ቆመው እንዲያዩ ቀጭን ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ፣ አራጆች - ተባባሪዎቻቸውን ጠርተው - ቤተ ክርስትያን ሲቃጠል፣ ዜጎች በገጀራ ሲሰቀሰቁ፣ ቤት ንብረት ሲጋይ፣ ትምህርት ቤቶች ሲቃጠሉ እገዛ እንዲያደርጉላቸው - መመርያ ሲሰጧቸው - መንግሥት መረጃ አልነበረውም ማለት አይቻልም። ሽብርተኞች ቤርጎና መኖርያ ቤት ተከራይተው እቅድ ሲነድፉና የሚገደሉ ሰዎች እንዲሁም የሚቃጠሉ ንብረቶችን ስም ሲመዘግቡ መንግስት አላውቅም ማለት አይችልም። መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ ኃላፊነቱን አልተወጣም። ዛሬ በኦሮምያ ክልል የሚኖሩ አማሮች፣ የሸዋ ኦሮሞዎች፣ ትግራዋዮችና ጉራጌዎችን ጨምሮ መላው የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ስጋት ላይ ናቸው።
መንግሥትና የጸጥታ አስከባሪዎች ባሉበት ኦነግ ሸኔ ይህን ሁሉ መከራ መፈጸሙ ብዙ ጥያቄዎችን ይጭራል። ይህን ሁሉ ሰቆቃ የሚያስተውልስ እንደምን ቆም መሄድ ይችላል? “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” ማለትስ አሁን ነው። ምን እንላለን፤ ማንስ ሕይወታችንን ይታደገን፣ ማንስ ለፍትህ ይጩህ ። “አቤቱ ጌታዬ ከዘር ፍጅት (Genocide)፣ ከመዓቱ ሰውረን” ብቻ እንጂ።