Tuesday, November 3, 2020

አይበቃም ወይ ?

 ሀገር ማለት ሰው ነው ያሉህን ተቀበል 

ሰው በሞተ ቁጥር ሀገሬ ሞተች በል 

😭😭😭😭😭😭😭

Monday, October 5, 2020

የሽግግር መንግስት ይቋቋም

 https://www.ethiopoint.com/amharic/archives/111515

የሽግግር መንግስት ይቋቋም

 “የሽግግር መንግሥት ይቋቋም” ከሚክያስ


የፓርቲ ድርጅቶችን ጠፍጥፎ በመስራት ረገድ እንደ ሕወሃት ያለ የጭቃ መሃንዲስ የለም። አማራውን ይወክላል የተባለው ኢህዲን ወይም ብአዴን ከመረሬ ጭቃ ነው የተሠራው። ኦሮሞውን ይወክላል የተባለው ኦሆዲድ ከቀይ አፈር ጭቃ ነው እነደ ቂጣ ተጠፍጥፎ የተጋገረው። የደቡቡ፣ የሶማሌው አጋር የተባሉት ሁሉ ካካባቢው ጭቃ ነው የተቦኩት። እነዚህ የጭቃ አጋሰሶች ከፊት ለፊት የሚታያቸውን መኖ እየተከተሉ ህወሃትን ለሰላሳ ዓመታት አገለገሉ። ሁሌ ጠፍጥፎ አደር መሆን የለምና፣ ሕወሃት ራሱ ጠፍጥፎ ከሰራው ማህል አንዱ የነቃው አደናግሮ ፈነገለው። “ጠፍጥፌ የሠራሁትማ ጠፍጥፎ አይሰራኝም” ሲል እልህ የተናነቀው ሕወሃት ወደ መቀሌ ፈርጥጦ በተራው ዋነኛ ተቃዋሚ ሆነ። አዲስ አበባን ፊንፊኔ እስከ ማለት የደረሰው ሕወሃት ራሱ ድሮ የሚፈጽማቸውን ሁሉ መቃወም የጀመረ ነፈዝ ሆኗል።

ዶክተር አብይ ኦህዲድን ለሁለተኛ ጊዜ ጠፍጥፈው ጠርበው ስሙን ኦዴፓ ብልጽግና አሉት። አዲሱ ኦዴፓ (ODP) ጠፍጣፊ ሆኖ ኢሕዴን-ብአዲንን እንደገና ጠፍጥፎ አዴፓ (ADP) ብልጽግና አለው። ኦህዴድ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ተጠፍጥፎ የተሠራው “አማራውን ወክያለሁ” እያለ የሚቃዠው የቀድሞው ኢሕዴን ሶስተኛ ጊዜው ነው ተጠፍጥፎ ሲሰራ። ኢሕዴን - አዴፓ ብልጽግና እስኪባል ድረስ ብዙ ጊዜ ተጠርቧል። “አማራው ጀግና ነው ጥፍጥፎች አይመሩትም” ያለው ጄኔራል በሴራ ከተወገደ በኋላ በታማኝናት የሚያገለግለው አዴፓ ዛሬ የኦዴፓ ካባ አልባሽ ሆኗል። ኦዴፓ ብልጽግና ባለጊዜና ተረኛ ሆነ።

ተረኛውን ባለጊዜውን ኦዴፓ (ODP) ብልጽግና ዶግ አመድ ለማድረግ የሚጥረው “ተጠፍጥፌማ አልሰራም” በሚለው አቋሙ የጸናው ሕወሃት ሌሎች የወንበር ሱሰኞችን እየገዛ በደሃው ሕዝብ ላይ በደሎችን እየፈጸመ ነው። የምስኪኑ አማራ ገበሬ ልጆች የሆኑ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎችን አሳፍኖ ከማስወሰድ አንስቶ በኦሮምያ ምድር የሚገኙ አማራና ኦርቶዶክስ ክርስትያኖች ለማውራት ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ በግፍ እስኪጨፈጨፉ ድረስ ሕወሃት ረዥም እጆች አሉት። ሕወሃት ግብረ አበሮቹን እያስተባበረ ኦዴፓ ብልጽግናን ፋታ አሳጥቶታል። “ሁለት ዝሆኖች ሲታገሉ” እንደሚባለው በሕወሃትና ብልጽግና መሃል ባለው የሥልጣን ትንቅንቅ መሃከል የተጎዳው አይዞህ ባይ፣ አዳማጭ፣ ተከላካይ የሌለው ሃገሬ ብሎ በየቦታው የሰፈረው አማራ ነው። እግዚአብሄር ግፉን በቃ እስኪል ድረስ አማራው እጆቹን ወደ ላይ ዘርግቷል።

ተረኝነት እንጂ ለውጥ በሌለበት ሁኔታ ቢዳክሩ ድካም ነው ትርፉ። “የሰበሩንን ሰበርናቸው” ከሚለው እስከ “ኦሮሞን እንገነባለን፣ ኢትዮጵያን እንደግፋለን” ድረስ የተረጨው ቅርሻት ሃገሪቱ አሁን ድረስ የቅርሻት መድሃኒት እንዳላገኘች ማሳያ ነው። በኦሮምያ ውስጥ ያለውን ሌብነትና ዘረፋ ማምከን ያልተቻለው ኦዴፓ ግድ ስለሌለው ነው። የኦሮምያ የስርቆት ባህል እንዲቀጥል የሚሹ ሁሉ - ጉዳይ አስፈጻሚ የሚባለው - ባለ ጉዳይንና የግብር ሰብሳቢዎችን፣ ባንኮችን፣ ማዘጋጃ ቤቶችን፣ ወዘተ፣ የሚያገናኘው የሙስና ድልድይ እንዲፈርስ አይፈልጉም። ተገልጋዩ ቢንገላታ ኦዴፓ (ODP) ብልጽግና ምን ቸገረው? “ግብርህ ስምንተ መቶ ሺህ ብር ነው - አራት መቶ ብር ሺህ ብር ላስደርግልህና አንድ መቶ ሺህ ብር ስጠኝ” የሚሉት ሶስተኛ ወገን መዝባሪ አስመዝባሪ ፋይል አጋቾች፣ የዓመታት የሌብነት ልምድ ስላላቸው እነሱን አደብ ለማስገዛ ኦዴፓ (ODP) ብልጽግና ቁርጠኝነት የለውም። ኦዴፓ ብልጽግና በከንቱ ስብሰባ ስም የሚባክነውን አላስፈላጊ ወጪ እንኳን የማስቆም ኃይል የለውም። የየቢሮዎቹን መዛግብት አቀማመጥ ሳይቀር የሚያውቁት የኦሮምያ ምድር ቀማኞች ለሆድ አደሩ ባለሥልጣን “መቶኛ ድርሻውን” እያስታቀፉ ፍትህን ያስጨፈልቃሉ፣ ድህነትን ያስፋፋሉ፣ ሥራ አጥነትን ያበዛሉ። ኦዴፓ-ብልጽግና የራሱን አባላት ጠባይ ሳያርም እንደምን ለውጥ ማምጣት፣ ፍትህን ማስፈን፣ ደሃውን ቀና ማድረግ ይቻለዋል?

ንጹህና አገር ወዳድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጅግ ጥቂት ስለሆኑ ነው ይህ ሁሉ ምስቅልቅል። አብዛኛው የሚንሰፈሰፈው ለወንበሩ ነው። ወንበሩን የፈለገው ሃገሪቱን በሥርዓት ለማስተዳደር ሳይሆን ተረኛ ሆኖ ለመመዝበር ነው። ስርቆትና ምዝበራ ነውር መሆናቸውን የሚያስተምር አንድ ኃይል ያስፈልጋል። መስረቅ፣ ቅሚያና ሙስና የምጣኔ ኃብት ስልት ወይም ከድህነት አበሳ መገላገያ የሚመስላቸው ዘራፊዎች ካልተማሩ አልያም ካልተወግዱ በቀር ሙስና እንደ ጦር ትሾላለች። ብናስተውል ግን ሠርቆ የከበረ ሁሌም ደሃ ነው። በቅሚያ ወርቆች ያጌጠች ሴት አያምርባትም። የመስቀል በዓል እንዳይከበር ተከልክሎ ለእሬቻ ቢፈቀድ እግዚአብሄር ያያል። የኢትዮጵያን ባንዲራ አትያዙ ብሎ ለኦነግ ባንዲራ ቢፈቀድ የሚጎዳው ራሱ ፈቃጁ አካል ነው። ቀኑን ጠብቆ ሁሉም እንደ ጠዋት ጤዛ ይረግፋል። ማንም በራሱ የሚመካ ሁሉ ፍጻሜው ከእግዚአብሄር መጣላት እንዳይሆን ቢጠነቀቅ ይሻለዋል።

ዶክተር አብይ ኢትዮጵያን ከወደዱ - አሁንም አልመሸም ትልቅ ታሪክ ሊከውኑ ይችላሉ። ዶክተር አብይ ይመለከተኛል የሚሉትን የፖለቲካና ሕዝባዊ ድርጅቶች፣ ምሁራን፣ በሕዝብ የሚመረጡ የሃገር ሽማግሌዎችንና አባ ገዳዎችን፣ አዛውንቶችንና የኃይማኖት አባቶችን፣ ንቁ ወጣቶችንና ታዋቂ ግለሰቦችን፣ ለሕዝብ ሲሉ እየታገሉ ያሉ ሃቀኛ መምህራን ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ተዋንያን፣ ከያንያን፣ ወዘተ፣ አሰባስበው መፍትሄ ሲያፈላልጉ ትልቅ ሥራ ሠሩ ማለት ነው። ማንም ነገ ለይስሙላ በሚዘጋጀው ምርጫ ላይ አሸናፊ ቢሆንም ኢትዮጵያን ፋታ አግኝቶ ሊያስተዳድራት አይችልም። ዶክተር አብይ - “ይቀናቀኑኛል” የሚሏቸውን የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች አስረው አሸናፊ ቢሆኑ ሕዝብ ወዶ ፈቅዶ የሚገዛሎት ንጉሥ አያደርጎትም። ሃገሪቱ መፍትሄ የምታገኘው በሳልና ማስተዋልን የለበሱ አዋቂ ሰዎች ተወያይተው፣ ተማምረው፣ ተማምነው ከራስ ወዳድነትና አድር ባይነት የጸዳ እውነተኛ የሽግግር መንግሥት ሲያቋቁሙ ነው። የሽግግር መንግሥቱ የሕዝባዊ መንግሥት መሠረትን ያነጥፋል። ኢትዮጵያ ከፍ አለች ማለት ይህን ጊዜ ነው።

ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች!

Monday, August 3, 2020

💚💛❤️

ቼ በለው  አባይ የግሌን 
ቼ በለው  ባልኩኝ የጋራ 
ቼ በለው  ካቃራት ምስር 
ቼ በለው  ግፍም ሳትፈራ 
ቼ በለው  የተቆጣ እንደው 
ቼ በለው  ፍቅር ታግሶ 
ቼ በለው  የሚባላ እሳት 
ቼ በለው  ይሆናል ብሶ
💚💛❤️

Saturday, July 25, 2020

የዘር ፍጅት (Genocide)! - አቤቱ ጌታዬ ከመዓቱ ሰውረን - ከሚክያስ

ሕወሃት አዲስ አበባ ከከተመበት ቀን ጀምሮ የታወጀው አማራውን ከምድረ ገጽ የማጥፋት ዶክትሪን ዶክተር አብይ ሥልጣን ላይ ሆነውም አልተገታም። ዛሬ ላይ ገሃድ የሆነው የዘር ፍጅትና አስቃቂ ግድያዎች የሕወሃት የዘር ፍጅት ምዕራፍ ቅጥያ ነው። የዛሬ ሠላሳ ዓመት ገደማ ጠባቂና ተከላካይ የሌለው ምስኪኑ አማራ በወያኔው ሹም ትዕዛዝ አርባጉጉና በደኖ ላይ ከገደል ተወርውሯል። ኦርቶዶክሱና አማራው ላይ ያነጣጠረው ይህ ዘርን የማጽዳት አረመናዊ ጭፍጨፋ ከቡራዩ እስከ አዲስ አበባ፣ ከአርሲ እስከ አዳማ፣ ከባሌ እስከ ሐረርጌ፣ ከሻሸመኔ እስከ አርሲ ነገሌ፣ ወዘተ፣ ተካሂዷል። አማራውና ኦርቶዶክስ ክርስትያኑ ላይ የደረሰው የዘር ፍጅት ናዚ ጀርመን እስራኤሎች ላይ ካደረገው እልቂት በዓይነት ይለያል።፣

አማራ ይህ ዓይነቱ ዘግኛኝ ግፍ የሚፈራረቅበት ሌሎች ያጡት ነገር ግን እርሱ ብቻ የጨበጠው ጥቅም ኖሮ አይደለም። አማራ እንደ ሌሎች ወገኖቹ ደሃ ነው። ታድያ ምን አጠፋ -እግዚአብሄርን ማምለኩ፣ ሃገርን፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራውን መውደዱ ነው ወንጀሉእንደው ለነገሩ አማራው ብቻ ነው ኢትዮጵያን የሚወደው?ኦሮሞው፣ ጋምቤላው፣ ወላይታው፣ ሲዳማው፣ ጋሞው፣ ቤንሻንጉሉ፣ ጉራጌው፣ ወዘተ፣ ሁሉም ኢትዮጵያን ይውዳል። ለምን ይሆን ታድያ አማራው ለእልቂት የተመረጠውን የተለየ በደል ሰርቶ ነው ሕወሃትና ኦነግ አማራው ሠለባ እንዲሆን የፈረዱትቅኝ ገዥዎች የተሸነፉት በመላው ኢትዮጵያዊ ትብብር ነው። አማራው ብቻውን አድዋ አልዘመተም። ግን ለምን ይሆን አማራው ላይ ብቻ እልቂት፣ ግድያ፣ እገታ፣ ማምከን፣ ንብረት ማቃጠል፣ ወዘተ፣ የተፈረደውበእርግጥ አማራው ላይ እልቂት እንዲፈጸም ሠይጣናዊ ሃሳቡን ያረቀቀው ወያኔ "ዘር ከዘር አፋጅቴ ኢትዮጵያን ለሺህ ዓመት በማን አለብኝነት እገዛለሁከሚል አላዋቂነት የተነሳ ነው። ወያኔ ይህን ድንቁርና የወረሰው ከቅኝ ገዥዎች ነው። ይህን አላዋቂነት ጽንፈኞችና አማራ-ጠል ምሁራን ተጋሩት። ይህን አላዋቂነት ሃገር እንድትፈርስ የሚፈልጉ ሁሉ ከአድማስ አድማስ አናፈሱት። በዘር እልቂት ሽፋን ሚኒልክ ቤተ መንግሥት መግባት የሚፈልጉ ሁሉ ዘረኝነትን በወጣቶች ዓዕምሮ ውስጥ እንዲያድር ብዙ ደከሙ።

ሃገር ጠሎች አማርኛን፣ የቅኝ ግዛት ሽንፈት ምልክት የሆነውን የሚኒልክን ሃውልት እንደጦር ይፈራሉ። አማርኛ እኮ የአማራ ብቻ ቋንቋ አይደለም። የሚኒልክ ሃውልት እኮ የኢትዮጵያ ብቻ መኩርያ አይደለም። መላው አፍሪካና በቅኝ ግዛት የማቀቁ ሃገሮች ሁሉ የሚኒልክ ሃውልትን ይወዳሉ። በብዙዎች የአፍሪካ ሃገራት እኮ በሚኒልክ ስም አደባባይ፣ መንገድ፣ አዳራሽ፣ ትምህርት ቤት፣ ወዘተ፣ ተሰይሟል። "የሚኒልክ ሃውልት ይፍረስየሚለውን የቅኝ ግዛት ሃሳብ በሞኝ ምሁራን ዓዕምሮ ውስጥ አስቀምጠው ሲዘርፉ የነበሩ ወያኔዎች የማታ ማታ የት ደረሱዛሬ በሕይወት ያሉት ወያኔዎች ወደ ቀልባቸው ተመልሰው በወገናቸው አምሃራው ላይ የደረሰው እልቂት ይከነክናቸው ይሆንእግዚአብሄር ይወቀው። አቶ ስብሃት "አማራና ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን አከርካሬአቸው ተሰብሯል፣ ከዚህ በኋላ አያንሰራሩምሲል የተናገረው አረፍተ ትዕቢት - "ነፍጠኞች የሠበሩን ቦታ ላይ ቆመን ነፍጠኞችን ሰብረናልወደሚለው አረፍተ-ከንቱ ማደጉ ያሳዝናል እንጂ የሳይንስ እድገት ማሳያ ጥበብ አይሆንም። ወያኔ ያበላሸውን ሥርዓት ዳግም ለማበጀት ግብረገብ ማስተማሩ እንጂ ማሳሳቱ ምን ይበጃልለዓመታት የተደከመባቸውን በጥቂት ደቂቃዎች በእሳት አጋይቶ ማውደም ሃይፐር ሶኒክ ጄት እንደ መሥራት የሚኮራቸውን ግፈኞች መክሮ ገስጾ መመለሱ እንጂ ማመጻደቁ ምን ይበጃል?እግዚአብሄር እኮ ሁሉን ያያል። አምላክ እኮ የምስኪኖች ዋይታ ይሰማል።

ባለፈው “ተከብቤአለሁ” ሳብያ የሞቱ ዜጎች ሃዘን ሳይወጣልን በሰሞኑ ጥቃት ሻሸመኔ እንደ ሶርያዋ አሌፖ ስትጋይ፣ ምስኪኖች እጅና እግራቸው ተቆራርጦ አቅመ ደካሞች ደግሞ በገጀራና ጦር ተሸቅሽቀው ተገድለዋል፣ አንድ ባለሉካንዳ ተገድሎ በሥጋ መስቀያ ሜንጫ ላይ ተንጠልጥሏል። ጥቃቱ ጅማንም መቷል። በሰሞኑ ፍጅት ባጠቃላይ ከ230ሰዎች በላይ ተገድለው ሌሎች 200 ያህል ሰዎች ቁስለኛና አካለ ጎዶሎ ሲሆኑ 250 መኪኖች ተሠባብረው፣ 20 ያህል ተቃጥለዋል። አረመኔዎች 35 ፎቆች እንዲሁም ከሺህ በላይ መኖርያ ቤቶች አቃጥለው ጨፍረዋል። በቦስንያ ጭፍጨፋ ሰው ተዘቅዝቆ አልተሰቀለም። አርመኖች ላይ በደል ሲፈጸም የሴት ልጆች ጡት አልተቆረጠም፣ ሰው ተዘቅዝቆ አልተሰቀለም። የአርሲ ነገሌውና የሻሸመኔው ውድመት ከሩዋንዳው እልቂት ጋር ሲነጻጸር እንኳን በዘግናኝነቱ ላቅ ይላል። የሰው ልጅ በፍቅርና በመተሳሰብ በሚኖሩባት የምድር ገነት ተብላ በምትወደሰው ኢትዮጵያ ኦነግ ሸኔ በአይዞህ ባዮቹ እየታገዘ ማንንም ሳይፈራ ጥቃት ፈጽሟል። እስላም ክርስትያን የሞሉባት ኢትዮጵያ ውስጥ ዘግናኝ እልቂት መፈጸሙ እጅግ ያስለቅሳል።

መንግሥት የዘር ፍጅት ሲፈጸም፣ ጥብቅ ቁጥጥር ባለማድረጉ ተጠያቂ ነው። ግፈኞች ደሞዝ የሚከፈላቸው ባለሥልጣኖችና ሥርዓት አስጠባቂዎች ቆመው እንዲያዩ ቀጭን ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ፣ አራጆች ተባባሪዎቻቸውን ጠርተው ቤተ ክርስትያን ሲቃጠል፣ ዜጎች በገጀራ ሲሰቀሰቁ፣ ቤት ንብረት ሲጋይ፣ ትምህርት ቤቶች ሲቃጠሉ እገዛ እንዲያደርጉላቸው መመርያ ሲሰጧቸው መንግሥት መረጃ አልነበረውም ማለት አይቻልም። ሽብርተኞች ቤርጎና መኖርያ ቤት ተከራይተው እቅድ ሲነድፉና የሚገደሉ ሰዎች እንዲሁም የሚቃጠሉ ንብረቶችን ስም ሲመዘግቡ መንግስት አላውቅም ማለት አይችልም። መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ ኃላፊነቱን አልተወጣም። ዛሬ በኦሮምያ ክልል የሚኖሩ አማሮች፣ የሸዋ ኦሮሞዎች፣ ትግራዋዮችና ጉራጌዎችን ጨምሮ መላው የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ስጋት ላይ ናቸው።

መንግሥትና የጸጥታ አስከባሪዎች ባሉበት ኦነግ ሸኔ ይህን ሁሉ መከራ መፈጸሙ ብዙ ጥያቄዎችን ይጭራል። ይህን ሁሉ ሰቆቃ የሚያስተውልስ እንደምን ቆም መሄድ ይችላል? “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” ማለትስ አሁን ነው። ምን እንላለን፤ ማንስ ሕይወታችንን ይታደገን፣ ማንስ ለፍትህ ይጩህ ። “አቤቱ ጌታዬ ከዘር ፍጅት (Genocide)፣ ከመዓቱ ሰውረን” ብቻ እንጂ።