Sunday, July 26, 2015
Thursday, July 23, 2015
አርበኞች ግንቦት ሰባትና ሊቀመንበሩ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ
አርበኞች ግንቦት ሰባትና ሊቀመንበሩ ዶክተር ብርሃኑ ነጋከሚክያስ ሙሉጌታ ግዛው
ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በወጣትነታቸው ዘመን እንደማንኛውም ወጣት በተማሪው ንቅናቄ የተሰለፉ፣ የኢሕአፓ የወጣቱ ክንፍ አባል በመሆንም ደርግን የታገሉ ኋላም ወደ ሱዳንና አሜሪካ የተሰደዱ የነጻነት ትግሉ አባወራ ናቸው። ዶክተር ብርሃኑ ደርግ ወድቆ ወያኔ ስልጣኑን ሲይዝ ሕዝቡን እውጭ ባካበቱት ልምድ ለማገልገል ፈቅደው ወደ ሃገራቸው ተመልሰው በዩኒቨርሲቲ ከማስተማር ጀምሮ በቅንጅት ፓርቲ ውስት በአመራሩ ውስጥ ጉልህ ተዋናይ እስከመሆን ድረስ አገልግለዋል። ቅንጅት አምባገነኑን ሥርዓት በሠላማዊ መንገድ በመታገል በአፍሪካ ምድር ለመጀመርያ ጊዜ ሕዝባዊ ምርጫ አሸናፊነቱን እንዲጎናጸፍ የበኩላቸውን አስተዋጾ አድርገው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እንዲሆኑ የተመረጡት ዶክተር ብርሃኑ ሥልጣኑን በሰላም ለማስረከብ ፍቃደኛ ባልሆነው ወያኔ ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር በእስር ቤት ተወርውረዋል። ከወራት እስር በኋላ የተፈቱት ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ወደ አሜሪካ ተመለሱ።
ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ወያኔ ስልጣኑን በሠላማዊ መንገድ ለማስረከብ ባህርይው እንደማይፈቅድለት ከተረዱ በኋላ ግንቦት ሠባት የዲሞክራሲንና ፍትህ ንቅናቄን፣ ከሌሎች ጓዶች ጋር በመሆን መሥርተው ሲያደራጁና በፋይናንስ ሲያጠናክሩ ቆይተው በቅርቡ ከአርበኞች ግንባር ጋር የተዋሃደውን የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄን ፍልሚያ ሊመሩ ወደ ኤርትራ ምድር ተጉዘዋል። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ወደ አስመራ ሲጓዙ የመን ላይ በወያኔ የተጠለፉት ሌላኛው ግንቦት ሰባትን አምጠው የወለዱ የኢትዮጵያ አንጡራ ልጅ ናቸው።
ዶክተር ብርሃኑ ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ የተለዩ አለመሆናቸውን ዘወትር ይናገራሉ። መማር ለሀገር ሕልውና ካልበጀ፣ ሕዝቡን ቀና ካላደረገ የጋን ውስጥ መብራት ሆኖ እንደሚቀር በየስብሰባው ይገልጻሉ። ዶክተር ብርሃኑን የሚያረካቸው የነጻነት ትግል እንጂ የሥልጣን መዳረሻው ወንበር ምቾት አይደለም። ይህ የዶክተር ብርሃኑ ነጋ የትጥቅ ትግሉን ለመቀላቀል ብሎም ለመምራት ወደ ኤርትራ ጉዞ በኢትዮጵያ ሕዝብ ሥልጣን ትግሉ ረዥም ጉዞ አንድ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ መክፈቱ ብቻ ሳይሆን ግንቦት ሰባት ለሕዝብ የገባውን ቃል ኪዳን ተራ በተራ መተግበሩን ይመሰክራል።
ወያኔ በሠላማዊ ትግሉ ፈጽሞ ስልጣኑን ማስረከብ እንደማይችል መረጋገጡ ሕዝቡ በአንድ ልብ የትጥቅ ትግሉን እንዲደግፍ ያደርገዋል። የአርበኞች ግንቦት ሰባት የሠሞኑ ማጥቃት ከትጥቅ ትግሉ በቀር ሌላ ፖለቲካዊ አማራጭ እንደሌለ በጽኑ ስለሚያሳይ ዳር የቆሙም ሆነ ፖለቲካ በሩቁ የሚሉ ሁሉ ሃገራዊ ድርሻቸውን ለማበርከት ይነሳሳሉ። የትጥቅ ትግሉን ለመቀላቀል ሠፊ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች ከስደቱ ውርደት ይልቅ የጦር ሜዳውን ጀግንነት ይመርጣሉ። ሳይወድ በግድ የወያኔውን ስልጣን አስጠባቂ የሆኑት የመከላከያ ሠራዊቱና የፖሊስ አባላት ሕዝባዊውን ትግል በፍቅር ይቀላቀላሉ። ሌላው ቀርቶ የሙስናው ጥቅም ተቋዳሾች የሆኑት ባለስልጣኖቹና ዘመዶቻቸው ሳይቀሩ ስህቶቻቸውን አርመው፣ የበደሉትን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀው ወያኔን አንቅረው በመትፋት የዘረፉትን የሕዝብ ሃብት በውዴታ ይመልሳሉ።
መልካም ፖለቲካ በሰዎች አመለካከት ላይ የተንሰራፉ ብዥታዎችን ታጠራለች። ፖለቲካ አይታመንም፣ አሜሪካ ተቀምጦ ትግል የለም፣ ወዘተ፣ ዓይነቶቹ ግራ አጋቢ ብዥታዎችን እያጠሩ፣ የትጥቅ ትግሉን በማደራጀት ወያኔን መሪር የሆነ ቀውስ ውስጥ የከተተው ብሎም ከሕዝብ ወገን ከተውጣጣው ጦር ጋር እንዲላተም ያደረገው እንደነ ዶክተር ብርሃኑ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌና መሠሎቻቸው ያበረከቱት ትዕግስትንና ብስለትን የተላበሰው በሳል የፖለቲካ ሂደት ነው። ፖለቲካ እጅግ ተለዋዋጭ መሆኗ ብቻ ሳይሆን አስተማሪም ነች። በአንክሮ ለተመራመራት ፖለቲካ የትላንቱን ስህተት አጉልታ እያሳየች ወደ ተሻለው አቅጣጫ የምትመራ ምስጢራው ኮምፓስ ነች። በአንክሮ ማየት የተሳነው ደግሞ ሁልጊዜ ወደ ታች፣ ወደ ቁልቁለቱ ይጓዛል። መልካም ፖለቲካ ትክክለኛውን መንገድ ስትጠቁም ሙስና ደግሞ ልቦናን ጋርዳ ወደ ገደሉ ታዳፋለች። እብሪተኛውን ወያኔ ባዶ ያስቀረው አላዋቂ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከጀርባው ልትወርድ ያልቻለችው አታላዩዋ፣ አዘናጊዋ ሙስና ነች። ወያኔው በሙስና የገነባውን ሕንጻ አንጋጦ ሲያይ ወይም ምቾቱ በተደላደለው እጅግ ውድ ዘመናዊ አውቶሞቢሉ ሲንሸራሸር አልያም ከፍ ዝቅ በሚለው አረግራጊው በኤሌክትሪክ ኃይል በሚሞቀውና በሚቀዘቅዘው ፍራሽ ላይ እንደተኛ ሕዝባዊው ሱናሜ ከተፍ ይልበታል።
የሁለት አስር ዓመቶቹ መልካምና ሠላማዊ የፖለቲካ ክንውኖች እንዲሁም ከታሪክ ሂደት መማር ያልቻለው "የመቶ ፐርሰንቱ" አሸናፊው ወያኔው ግትር ባህርይ ይህን የትጥቅ ትግል ወልዷል። ፍልሚያው በግለሰቦች አስተሳሰብ ላይ ሠፍነው የነበሩትን አንዳንድ ጥርጣሬዎች አስወግዶ መላውን ሕዝብም ሆነ የፖለቲካ ንቅናቄዎችን እንዲሁም የትግል ግንባሮችን በቅጡ ያዋህዳል።
ሁሉም በጦርነት ተሠልፎ ተዋጊ ሊሆን አይችልም። ጀግንነት፣ ተጋድሎና መስዋዕት ለመክፈል ከፊት መቅደም ከእግዚአብሄር የሚበረከት ፀጋ ነው። ወታደርነት እልህ አስጨራሽ፣ ጀግንነት ደግሞ ከጽናት የምትመነጭ አኩሪ ተግባር ነች። ሁላችንም በዚህ አኩሪ ተግባር ውስጥ መሰለፍ ባንችልም እንኳን ደጀን መሆን አያቅተንም። መናቆርን፣ መጠላለፉን አስወግደን ሁላችንም ፊታችንን ወደ ጦሩ ግንባር በማዞር የሞራል፣ የቁሳቁስና የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅብናል። በአንድም በሌላም ከመሳተፍ ተቆጥቦ የነጻነቱን ትግል አለመቀላቀል ወይም ወስልቶ መቅረት በግለሰቡ ዓዕምሮ ላይ ህፍረት ሆና ተለጥፋ የምትቀር የታሪክ ጥላሸት ነች። ይህች በሁሉም መስክ ክብር የነበራት ውድ ኢትዮጵያችንን ያዋረደውን ወያኔን መፋለም ታላቅ ክብር ነው።
በአርበኞች ግንቦት ሠባት አባልነት ተመዝግበን ትግሉን የመቀላቀል እድል የተጎናጸፍን ሁሉ ሌሎችም የኛን አርዓያ ተከትለው ሃገራዊ ድርሻቸውን የማበርከቱ እድል እንዲገጥማቸው ልባዊ ምኞታችንን እንገልጻለን። በዚህም ይሁን በዚያኛው መሰለፍ፣ የነጻነት ትግሉን የሚያግዝ አንዲት ጠጠር መወርወር ወይም የሕዝቡን መሠረታዊ መብቶች የሚያስጠብቀውን ትግል ከመቀላቀል የበለጠ ሌላ ጣፋጭ ነገር የለም።
አርበኞች ግንቦት ሰባት ያሸንፋል፤ ሕዝብ ያሸንፋል፤ አምባገነንነት በትግል ይወገዳል
Sunday, July 19, 2015
የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ነአምን ዘለቀ አዳዲስ ፎቶዎች ከአስመራ (ይናገራል ፎቶ)
ትናንት ዘ-ሐበሻ በሰበር ዜና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ነአምን ዘለቀ አስመራ መግባታቸውን መዘገባችን ይታወሳል:: በዚህ መሰረት የነዚህ አመራሮች ፎቶ ግራፎች ከአስመራ ደርሰውናል::
ዶ/ር ብርሃኑ ኤርትራ በገባ በጥቂት ሰዓታት ልዩት የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ፖለቲካ መምሪያ ህዝብ ግንኙነት ክፍል ወደሚገኝበት ቦታ በማምራት ከህዝብ ግንኙነት ክፍሉ አርበኛ ታጋዮች ጋር ምሳ በልተዋል:: ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ለህዝብ ግንኙነት ክፍሉ አርበኛ ታጋዮች ባስተላለፉት መልዕክት
“ከሁሉም ነገር ዓላማ ያስተሳሰረው ስለሚልቅ፤ ለእኔ ለአገሩ ህይወቱን መሰዋዕት ለማድረግ ከተዘጋጀ ሰው የሚበልጥ ምንም ነገር በምድር ላይ ባለመኖሩ ወደ እናንተ መጥቻለሁ፡፡ የመጣሁትም እናንተን ለማስተማር ሳይሆን ከእናንተ ለመማር ነው… ለነፃነታችን አብረን እንሞታለን…” ብለዋል::

- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/45185#sthash.kwAKZktj.dpufዶ/ር ብርሃኑ ኤርትራ በገባ በጥቂት ሰዓታት ልዩት የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ፖለቲካ መምሪያ ህዝብ ግንኙነት ክፍል ወደሚገኝበት ቦታ በማምራት ከህዝብ ግንኙነት ክፍሉ አርበኛ ታጋዮች ጋር ምሳ በልተዋል:: ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ለህዝብ ግንኙነት ክፍሉ አርበኛ ታጋዮች ባስተላለፉት መልዕክት
“ከሁሉም ነገር ዓላማ ያስተሳሰረው ስለሚልቅ፤ ለእኔ ለአገሩ ህይወቱን መሰዋዕት ለማድረግ ከተዘጋጀ ሰው የሚበልጥ ምንም ነገር በምድር ላይ ባለመኖሩ ወደ እናንተ መጥቻለሁ፡፡ የመጣሁትም እናንተን ለማስተማር ሳይሆን ከእናንተ ለመማር ነው… ለነፃነታችን አብረን እንሞታለን…” ብለዋል::

Subscribe to:
Posts (Atom)