Thursday, November 27, 2014

"ሕዝባው መንግስት"፣ "ሕዝባዊ መፈናቅል" ወይንስ "ሕዝባዊ መፍረስ"

"ሕዝባው መንግስት"፣ "ሕዝባዊ መፈናቅል" ወይንስ "ሕዝባዊ መፍረስ"
ሚክያስ ሙሉጌታ ከ ኖርዌ
ድሮ ከዘውዱ መገርሰስ በፊት አዲስ አበባ እንደህ እንዳሁኑ ጭንቅንቅ ያላለች ለመሆኗ ትላልቆች ሲናገሩ እሰማለሁኝ። ብዙ
ሰዎች እርስ በእርሳችን እንተዋወቅ ነበር፣ ያለው ለሌለው ያዝናል፣ አውደ አመቱን በጋራ እናከብራለን ይላሉ። ቤት ገብቶ
የሚዘርፍ ሌባ ቀርቶ የተሰጣን ልብስ እንኳን ከውጭ አንስቶ የሚሰወር ወስላታ እምብዛም አይታይም ይላሉ። ሁሉም
በአቅሙ ሰርቶ ስለሚኖር የሰው እጅን መመልከት ነውር እንደነበርም ያወሳሉ። ሕዝቡ እግዚአብሄርን በጽኑ ያመልካል፣
በኢትዮጵያዊነቱ ይመካል፣ ባንዲራውን ይወዳል፣ ንጉሱንም ያከብራል፣ እያሉ ትላልቆቹ ዘወትር ሲያወሩ በጽሞና
አዳምጣለሁኝ።
እኔ የማውቃት አዲስ አበባ ግን ታላላቆቼ እንደሚያወሩላት አይደለችም። ምንድነው ምክንያቱ አልኳቸው? "ቀድሞ
ክርስትያኑና እስላሙ ተፋቅሮ የሚኖርባት፣ ባህልና ወጉ የሚናፍቁባት፣ ግብረገብነቱና ጨዋነቱ ጥልቅ የነበሩባት፣ የምሁሩ
እውቀትና የሕዝቡ ማስተውል እንደ እንቁ የሚብለጨለጩባት፣ ኪነቱ፣ ቴያትሩና ስነ ጥበቡ እውነትንና እምነትን
ሲያንጸባርቁባት የነበረችው አዲስ አበባ ዛሬ በክፋት ሠራዊትና በሙስና ባለሃብቶች በመወረሯ ነዋ" አሉኝ። በእርግጥ እኔም
እንደታዘብኩት የአዲስ አበባ መሬት ካቅሟ በላይ በስርቆት በተገነቡ ሕንፃዎች፣ በዳንኪራ ቤቶች፣ መሸታ ቤቶች፣ ቅባት
ቤቶች፣ የውበት ሳሎኖች፣ ላውንደሪዎች፣ መኪና አከራዮች፣ ወዘተ ተጨናንቃለች።
የኢጣልያ የቅኝ ገዢነት ሕልም ለማብከን መኳንንቱ የመከሩበት የእምዬ ሚኒልክና የነብር አራስዎ እቴጌ ጣይቱ መናኸርያ
ያ ታላቁ ቤተ መንግስት ኢትዮጵያን በማይወዱት ሰዎች ተይዟል። የንጉሠ ነገስቱ ኃይለሥላሴ ማደርያ ኢዮቤልዩ ቤተ
መንግስትም ተደፍሯል። ደርግ ታላላቆቹ የሀገር ኃብት የነበሩትን ወደር የለሽ ምርጥ ምሁራን ቢገድልም አብዛኛዎቹን ንጉሱ
ያስተማሯቸውን ብቁ ምሁራን ተጠቅሞባቸው ነበር። ዛሬ ለየት ያለ ነው። ብቃቱ ፈጽሞ የሌላቸው የወያኔ የጫካ ሽፍቶች
የመንግስት መዋቅሩን ሲያዛንፉ አዲስ አበባ ዝም ብላለች። ማስተዋልና ጥበብ የሌላቸው ሁሉ ስልጣነ-መንግስቱን
ሲቀልዱበት አዲስ አበባ እንዴት እንዳስቻላት አላውቅም። ሌላም ጉድ አለ። የእግዚአብሄር ሰዎች የነበሩት ፓትርያርኮቹ
አቡነ ቴዎፍሎስ፣ አቡነ ተክለሃይማኖትና አቡነ መርቆርዮስ በታጋዩ አባ ጳውሎስ ሲተኩ ሕዝበ ክርስትያኑ በፍርሃት ተውጦ
ስልጣነ-ክህነቱንና ቅዱስ ሲኖዶሱን አስደፍሯል።
አዲስ አበባ ከየአራቱ ማዕዘናት የተሰባሰቡት የእትዮጵያ ሕዝቦች ባንድነት የሚኖሩባት ማዕከል በመሆንዋ የሀገሪቱን
ፖለቲካዊ ጥያቄዎችንም ለመንግስት የምታቀርበውም እሱዋው ነች። ቀደም ሲል በመላ ሃገሪቱ የሚገኙት ተማሪዎች
የንጉሱን አስተዳደር በመቃወም እጅግ እልህ የተሞላበት ትግልን ማድረጋቸው ሲታወስ፣ ለመንግስቱ ቅርበት ያላቸው
የአዲስ አበባው ተማሪዎችም ደግሞ ስርዓቱ ማስተዳደር እስቂያቅተው ድረስ ተናንቀውታል። በወሬ የምሰማው ''መሬት
ላራሹና" - "ሕዝባዊ መንግስት" ይመስረት መፈክሮች - መፈክሮች ብቻ ሳይሆኑ የታጋዩ ልበ ሙሉነትንን ማንጸባረቅያ
የሕዝቦች ሙሉ መብት እንደነበሩ ነው። ታጋዩ በየተራ ሲሞት ጥያቄዎቹ ግን እስካሁን መልስ አላገኙም። ያለፈው ወጣት
መሬት ላራሹ በማለቱ በንጉሱ ወታደሮች ተደብድቧል ተብሏል። ቀጥሎም ሕዝባዊ መንግስት በማለቱ በደርግ ቀይ ሽብር
ተገድሏል አሉ። የዘንድሮው በኔ ዘመን የተከሰተው ለየት ያለ ነው። ወጣቱ "ስብዓዊ መብት ይከበር" - "ሕዝባዊ
መንግስትም" እንዳይል ታፍኖ ስለ ስደት ብቻ እንዲያውጠነጥን ተደርጓል። እነአንዷለም፣ እስክንድርና ርዕዮት የመሳሰሉት
ብቸኛ ቆራጦች የቀድሞውን ወጣት ታሪካዊ አደራ ተሸክመው ሕዝባዊ መንግስት በማለታቸው ቃሊቲ ተወርውረዋል።
ከላይ በጽሁፌ ላይ እንደጀመርኩት አዲስ አበባ ዛሬ የተጨናነቀችው በተፈናቃዮችና በወሮበሎች ብዛት እንጂ የልማቱ
እንቅሳቃሴ በወለዳቸው ሠራተኞች አይደለም። አዲስ አበባን ጨምሮ ሌሎች ከተሞች ሳይቀሩ በጎዳና ተዳዳሪዎች፣ በሴተኛ
አዳሪዎች፣ በልመናና በሸክም በሚተዳደሩ፣ ጥቃቅን ሥራዎችን በሚፈልጉ ችግረኞች፣ ትምህርታቸውን በጨረሱ ሥራ
አጦች፣ በቀማኞችና ማጅራት መችዎች፣ በወያኔው ደህንነቶችና ፖሊሶች፣ ከተለያዩ ሀገሮች በመጡ ሴት አሳዳጆች፣ ጎጂ
ዕጾችንና ጫትን በሽያጭ በሚያስፋፉ ወሮበሎች፣ የሀገሪቱን ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ከሀገር በሚያስወጡ ዘራፊዎች፣
ሴት እህቶቻችንን ለአረቡ ሀገራት በሚያከፋፍሉ ደላሎች፣ በኮንትሮባንድ ሥራ በተሰማሩ አታላዮች፣ ወጣቱን ለስደት
በሚያሰማሩ አስኮብላዮች፣ ወዘተ ተሞልተዋል። በንጉሱ ዘመንም ሆነ በደርግ ዘመን ሕዝቡም እንዳቅሙ በልቶ ያድር ነበር
ይባላል። ዛሬ ግን ተጠቃሚዎቹ የሀገሪቱን ኃብትና ቅርስ መዝባሪዎቹ፣ ሙስናውን ከመጠን በላይ ያደለቡት ባለስልጣኖቹና
እነሱን ተገን ያደረጉት ወገነተኛ ነጋዴዎችና ዘራፊዎች ሲሆኑ ሕዝቡ ግን በረሃብ እየተቀጣ የብቀላ ርምጃ እየተወሰደበት
ነው።
ወያኔ ብዙዎችን ከቀያቸው ወይም ከሰፈራ ጣብያቸው እያፈናቀለ በየከተሞች እንዲሰበሰቡ ያደርጋል። የጋምቤላ ሕዝብ
መሬት ለሕንዶቹ ተሰጥቷል። የኦሞ ሸለቆው ድንቅ ሕዝብ መሬት እየተቀማ ለባዕዳኑ ሊሰጥ ነው። የአፋሮቹም መሬት
በሸንኮራ እርሻ ሳብያ እየተቀማ ነው። ወያኔ ዋልድባ የመሳሰሉትን ገዳማትን በማፍረስ ክርስትያኑን ሳይቀር በማፈናቀል ላይ
ይገኛል። በበደኖና በአርባጉጉ እንዳላስጨፈጨፉት ሁሉ ከደቡብ ኢትዮጵያ ቤንች ማጂ ዞን ጉራ ፋርዳ ወረዳ ለቀህ ውጣ
በማለት ይህንኑ መከረኛ አማራ እፈናቀሉት። ይህ ሁሉ ችግረኛ ሕዝብ ከተሞችን እንዲያጨናንቅ ሆን ተብሎ የሚሰራ ራሱን
የቻለ የወያኔው ሕዝብን የማፈናቀል ሥራ ከግፍ አገዛዙ መርሃ ግብር አንዱ ነው። ዓላማው ሕዝቡ በመንግስቱ ላይ
ከመነሳቱ በፊት በወሮበሎቹና ዘራፊዎቹ እርስ በእርሱ እንዲጨራረስ የተወጠነ ሰይጣናዊ ተልዕኮ ነው። ወያኔ በቅንጅቱ
ከተሸነፈ በኋላ ውስጥ ውስጡን ሲሰራው የነበረው ይህ ሕዝቡን የማፈናቀሉ ሥራ ድህነትን በየገጠሩ ማስፋፋትና ማህበራዊ
ቅራኔዎችን በከተሞች በማባባስ የአገዛዝ ዘመኑን ማስረዘም ነው። ባጠቃላይም ወያኔ ከተሞችን እንደ ኮንሴንትሬሽን ካምፕ
በመጠቀም ገጠሪቱን ኢትዮጵያ ላባዕዳኑ ኃይል በመሸጥ ላይ ነው።
አቶ መለስ የሀገሪቱን ችገር እኮ አስቀድመው ራሳቸው ነግረውን ነበር። "እድላችን ሆኖ ጠንካራ ተቃዋሚ አላገኘንም" -
ነበር ያሉት። አባባላቸውን ጠልቆ ሲረዱት እርሳቸው ወንበሩን በመቆናጠጣቸው ተቃዎሚዎችን ማንም እንደማይረዳ
የሚጠቁም ነበር። ቀጥለውም " አዲስ አበባ ፎቅ በፎቅ ሆናለች እየተባል ከዳር ዳር ይወራል - በእርግጥ ማንም ከደረጃ
በታች የሆነ ፎቅ በዘመናዊ ፎቅ ሲተካ የማይወድ የለም - ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ፎቅ ማህል አንድ ሶስተናው እንዱስትሪ
ቢሆን ኖሮ በልማቱ ላይ ከፍተና እድገት ያሳይ ነበር" - ብለዋል። ንግግራቸው ሕዝቡ ላይ ለማሾፍ ብቻም አይደለም። ፎቁ
በሙስና ሲገነባ ዝም ብለው ችግሩ ሲባባስ ማማሃኛ ፈለጉ። ችግሩን ወያኔ ሆን ብሎ የፈጠረው እንዳይመስል የማደናገርያ
የፖለቲካ ስልት ተጠቀሙ። ከምርጥ ንግግሮቻቸው ማህል ግን ይህን አባባላቸው ሁላችንንም የሚያነቃ መሆን ይገባዋል።
"መሬቱን ሊያለማ የሚመጣው አረቡ፣ ቱርኩና ሕንዱ ነው። ወደድንም ጠላንም ነገ ሀገር የሌለን ባይተዋር ነው
የምንሆነው" – ብለዋል። ወያኔዎቹ አስተዳደሩ ሲያቅታቸው ሀገሪቱን ለባዕድ ሸጠው ወይንም ኢትዮጵያን ለማፍረስ
ላደፈጡ ጠላቶችዋ አሳልፈው ሰጥተው ሕዝቡን ለመከራ አጋልጠው እነሱም ዶግ አመድ ሆነው እንደሚቀሩ አቶ መለስ
ተንብየው እስከወድያኛው አሸለቡ።
እድላችን እንዳይሰምር ሆኖ የሕዝባዊ መንግስት ጥያቄአችን እስካሁን መልስ ሳያገኝ ወደ ሕዝባዊ መፈናቅሉ አሸጋግሮናል።
ሕዝባዊ መፈናቅሉ ወደ ሕዝባዊ መፍረስ ሊያሸጋግረን ጥቂት ይቀራል። የዘመናቱ ባሕላዊው የዘውድ ሥርወ መንግስትና
የሀገር ሠራዊት ተንዷል፣ የሀገር ጥቅምና ሕልውና አስከባሪዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን በኢአማኞችና
ዓለማዊ ሴረኞች ተመዝብራለች። በደሙና በስጋው ዋጅቶ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ያስጠበቀው
ኢትዮጵያዊውን ልጅና የልጅ ልጆች ማፈናቀሉና ማሰደዱ ሀገሪቱን የማፍረሱ ቀጣይ ምዕራፍ ሆኗል። ዛሬ ከመንግስት
ሥልጣን ጠያቂነት ወደ ታች ወርደን ሀገርን ወደ ማዳን ደረጃ ተሸጋግረናል። ኢትዮጵያ ስትዳከም ፈንጠዝያው
የምዕራብያኖቹ ወዲህም የአረቦቹ ነው። ወያኔ የምዕራቦቹና አረቦቹ ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴ እንጂ እንደ ኢትዮጵያ
ሕዝብ ተወካይ ሲሰራ አልቻለም።
ከዚህ በኋላ ምን አይነት የትግል ስልት መከተል እንደሚኖርብን ግራ ተጋብተናል። የሃገሪቱ መፍረስ ግን የደቡቡን ሕዝብ፣
ኦሮሞውን፣ ትግሬውን፣ አማራውን፣ ጋምቤላውን፣ አፋሩን፣ ኦጋዴኑን፣ ባጠቃላይም መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚመለከት
ትልቅ አደጋ እንደሆን ልንረዳው ይገባናል። ጥያቄአችን የዲሞክራሲና የሕዝባዊ መንግስት መሆኖ ቀርቶ ሀገር የማዳኑ
ሆኗል።
እነዚህኑ መከራዎችና ግፎችን አስመልክቶ ብዙ ተጽፏል። ብዙ ውይይቶች ተደርገውበታል። በሀገር ቤት በሚኖሩም ሆነ
በውጭው በሚኖሩ ምሁራንም ብዙ ትችቶችና የተቃውሞ ጽሁፎች ቀርበዋል። ይህ ሁሉ የሰላም ትግል ወያኔ ሥርዓቱን
እንዲያሻሽል ወይም ሕዝብ በመረጠው መንግስት እንዲተካ ነበር። ግን ፈቀቅ ያለ ነገር የለም። የዋጋው ግሽበትና የድህነቱ
መስፋፋት ሕዝቡን አዳሽቆታል። ሕዝባችን ተሰዶ ሊያልቅ ነው።
ኢትዮጵያውያን ሁላችን ሃገር ከመፍረሷ በፊት አንድ ሃሳብ አንድ ልብ ሆነን አገርን ለማዳን በቆራጥነት እንዳይነሳ
ያላስቻለልን መንፈሳዊ ብክለት በቅጡ ልንመረምር ይገባል።
ሕዝባዊ መንግስት ስንል ስንጮህ የነበርን እንደዋዛ ሕዝብ የማፈናቀሉን የጉራፈርዳንና የቤንሻንጉሉ ፖለቲካን በአይናችን
ተመለከትን። ነገን ብንጠብቅ የባሰ ነው። ዛሬውኑ በአንድነት ተነስተን ሕዝባዊ መፍረሱን መታደግ አለብን።
በቸር እንሰንብት
ሚክያስ ሙሉጌታን በዚህ አድራሻ ማግኘት ይቻላል michyas.ethio@yahoo.com

ESAT Daily News Amsterdam November 26 2014 Ethiopia | ESATTUBE

ESAT Daily News Amsterdam November 26 2014 Ethiopia | ESATTUBE

Wednesday, November 26, 2014

ታሪክን ማደብዝዝም ማጥፋትም አይቻልም!

ታሪክን ማደብዝዝም ማጥፋትም አይቻልም!

ታሪክን ማደብዝዝም ማጥፋትም አይቻልም!

Nov 23, 2014
በአለማችን በተለይ አፍሪካ ዉስጥ የአገርን ብሄራዊ ኃብት የሚዘርፉ፤የህዝብን መብት የሚረግጡና አገርን እነሱ ባሰኛቸዉ አቅጣጫ ብቻ ይዘዉ የሚነጉዱ አያሌ ፈላጭ ቆራጭ መንግስታት አሉ። እነዚህ ህዝብን የሚበድሉ መንግስታት ሁሉም በጥቅሉ አምባገነን ይባሉ እንጂ በመካከላቸዉ ጎላ ብሎ የሚታይ ትልቅ ልዩነት አለ። ሀኖም የቱንም ያክል ልዩነት ቢኖርም እንደ ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች እንመራዋለን የሚሉትን ህዝብ የሚንቁና የኛ ነዉ የሚሉትን አገር የሚጠሉ አምባገነን መንግስታት የሉም፤ በታሪክም ኖረዉ አያዉቁም። አምባገነን መንግስታት የስልጣን ዘመናቸዉን ለማራዘምና ከስልጣን ጋር ተያይዞ የሚመጣዉን ክብር፤ ዝናና ጥቅማ ጥቅም እንዳይቋረጥ ሲሉ የሚቃወማቸዉንና ለስልጣን ዘመናቸዉ አደጋ ነዉ የሚሉትን ሁሉ ያስራሉ፤ ይደበድባሉ ወይም ይገድላሉ። እነዚህን ነገሮች የወያኔ መሪዎችም ያደርጋሉ፤ ነገር ግን በወያኔና በሌሎቹ አምባገነን አገዛዞች መካክል እጅግ በጣም ትልቅ ልዩነት አለ። ለምሳሌ ወያኔዎች ዘረኛ አምባገነኖች ናቸዉ፤ የወያኔ መሪዎች ኢትዮጵያን እንደ ጥገት ላም አንጂ እንደ አገራቸዉ አይመለከቱም። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያን፤ ህዝቧንና ታሪኳን ይንቃሉ፤ ያንኳስሳሉ።
ባለፉት አምስትና ስድስት አመታት በግልጽ እንደተመለከትነዉ የወያኔ መሪዎች የኢትዮጵያን ገበሬ ከመሬቱ አፋናቅለዉ ለምለም መሬቱን ለባዕዳንና ለህወሓት የጦር መኮንኖች ሰጥተዋል። መሬቴንና ቤቴን አልለቅም ብሎ የተቀናቀናቸዉን ደግሞ በጅምላ ገድለዋል። በከተሞች ዉስጥም ከተሜዉን ምንም ካሳ ሳይከፍሉት ዕድሜ ልኩን ከኖረበት ቤቱ እያፈናቀሉ ከነቤተሰቡ ሜዳ ላይ ጥለዉት መሬቱን ባለኃብት ለሚሏቸዉ የወያኔ ባለሟሎች ሰጥተዋል። በአጠቃላይ የወያኔ መሪዎች በኢትዮጵያ አንድነት፤ በታሪኳና በህዝቧ ላይ እንዲህ ነዉ ተብሎ ለመናገር የሚዳግት ትልቅ በደል ፈጽመዋል። ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች በእናት አገራችን ላይ ያደረሱት በደል ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለምና ዛሬ ወደዚያ ዝርዝር ዉስጥ አንገባም፤ ዛሬ ትኩረት የምንሰጠዉ ወያኔ ደግሞ ደጋግሞ ከዘመተባቸዉና ሙሉ ኃይሉን ካሳረፈባቸዉ የአገራችን እሴቶች አንዱ ታሪካችን ነዉና የዛሬዉ ቆይታችን በዚሁ በታሪካችን አካባቢ ይሆናል።
ታሪክ በአንድ አገር ዉስጥ እያንዳንዱ ትዉልድ ከሱ የቀደመዉ ትዉልድ በግል፤ በቡድንና በማህበረሰብ ደረጃ የተጓዘበትን መንገድ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ካለፈዉ የምንማርበትና የወደፊቱን ጉዟችንን ለመጀመር በመረጃነት የሚያገለግለንን እዉቀት የምናገኝበት የጥበብ ድርሳን ነዉ። የማንም አገር ታሪክ ዉብ ሆኖ የሚያምርና የማያምር ሁለት ገጽታዎች አሉት፤ የማያምረንን የታሪክ ጠባሳ ወደ ኋላ ሄደን ማከም በፍጹም እንደማንችል ሁሉ የወደፊቱን ታሪካችንንም የብዙ ማህበረሰባዊ መስተጋብሮች ዉጤት ነዉና ያሰኘንን ቅርጽና ይዘት ልንሰጠዉ አንችልም። የታሪክ ዋናዉና ትልቁ ቁም ነገር የታሪኩ ባለቤት የሆነዉ ማህብረሰብ እራሱን ወደ ኋላም ወደ ፊትም የሚመለትበት መስኮት መሆኑ ነዉ። ምንም አይነት ታሪክ የሌለዉ ህብረተሰብ የለም፤ ካለም ከየት አንደመጣና ወዴት አንደሚሄድም አያዉቅም።
አገራችን ኢትዮጵያ ረጂምና ጥንታዊ ታሪክ ካላቸዉ ጥቂት አገሮች ዉስጥ አንዷ ናት። ይህ ረጂም ታሪካችን ደግሞ አንገት ቀና የሚያስደርግ የድልና የገድል ታሪክ አንደሆነ ሁሉ አንገት የሚያስደፋ የግፍና የበደል ታሪክም አለበት። የዛሬዉ ትዉልድ ኢትዮጵያዊ ካለፈዉ ታሪኩ ከበደሉም ከገድሉም ተምሮ የወደፊት አካሄዱን ከሞላጎደል መቆጣጠር የሚችል እድለኛ ትዉልድ ነዉና አባቶቹ ባቆዩለት ታሪክ ሊኮራ ይገባል። አንድ ህዝብ በታሪኩ እንዲኮራ ደግሞ ታሪኩ በተደጋጋሚ ሊነገረዉ ሊተረክለትና በጽሁም መልክትም በገፍ ሊቀርብለት ይገባል። የአገራችን የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ለዚህ የታደለ አይደለም ፤ ምክንያቱም እንመራሀለን የሚሉት መሪዎቹ ታሪኩን የሚያንቋሽሹና የሚንቁ መሪዎች ናቸዉ።
ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ካደረሱትና ዛሬም በማድረስ ላይ ካሉት በደሎች አንዱና ዋነኛዉ የኢትዮጳያን ታሪክ ለባዕዳንና የታሪኩ ባለቤት ለሆነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ አሳንሰዉና እንደ ተራ ዕቃ አቃልለዉ ማቅረባቸዉ ነዉ። የወያኔ መሪዎች አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ መጀመሪያ ከተናገሯቸዉ ንግግሮች አንዱ የኢትዮጵያን ህዝብ ታሪክ የመቶ አመት ታሪክ ነዉ ያሉት አስቀያሚ ንግግር ነዉ። በዚህ አባባል ላይ የጸና አቋም ካላቸዉ የወያኔ መሪዎች ዉስጥ ዛሬ በህይወት የማይገኘዉ መለስ ዜናዊና ጓደኛዉ ስብሐት ነጋ ዋና ዋናዎቹ ናቸዉ። የሚገርመዉ እነዚህ የኢትዮጵያን ታሪክ በአንድ መቶ አመት የወሰኑት ሁለት ግለሰቦች የተወለዱት የኢትዮጵያ ህዝብ የዛሬ 119 አመት በአፄ ሚኒልክ መሪነት ወራሪዉን የጣሊያን ጦር አይቀጡ ቅጣት በቀጡበት አድዋ ዉስጥ ነዉ።
ወያኔ ካለፈዉ መስከረም ወር ጀምሮ ባደበዘዘዉ ቁጥር እያሸበረቀ ያሰቸገረዉን የኢትዮጵያ ታሪክ ለማቆሸሽ ጠባሳዉ ከትዉልድ ወደ ትዉልድ የሚተላለፍ የክፋት ስራ እየሰራ ነዉ። ኢትዮጵያን የመሰለ ባለታሪክ አገር ገድሎ ለሞተዉ ዘረኛ ሰዉ ትልቅ ማዕከል በህዝብ ገንዘብ የሚያሰሩት የወያኔ መሪዎች ማስቀመጫ ቦታ ጠፋ እያሉ አያሌ ብርቅ የሆኑ የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሀፍትን ከወመዘክር አይወጡ በችርቻሮ እየሸጡ ነዉ። እነዚህ ወያኔ የሚሸጣቸዉ መጽሐፍት የተጻፉት በተለያዪ ዘመናት ወደ ኢትዮጵያ መጥተዉ በነበሩት የእንግሊዝ፤ የፈረንሳይ፤ የጣሊያን፤ የስፔንና የጀርመን የታሪክ ጸሐፊዎች ነዉ። ከሰሞኑ ከአዲስ አበባ የሚመጡ ዜናዎች እንደሚያመለክቱት ወያኔ በዉጭ አገር የታሪክ ጸሐፊዎች የተጻፉትን የታሪክ መጽሐፍትና ተጠረዝዉ የተቀመጡ ቆየት ያሉ ጋዜጣዎችን በርካሽ ዋጋ እየቸበቸቡ የግሮሰሪ ዕቃ መጠቅለያ አድርጓቸዋል።
ይህንን አሳፋሪ የሆነ የወያኔ የመጽሐፍ ሽያጭ እንደ ተራ ወንጀል የምናልፍ ኢትዮጵያዉያን ካለን እጅግ በጣም ተሳስተናል። ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች የሚሰሩትን ስራ አበክረዉ የሚያዉቁ ሰዎች ናቸዉ፤ እያሰሩ ያሉት ስራ ደግሞ ግልጽ ነዉ። ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች የተጻፈ ታሪካችንን ብቻ ሳይሆን እያወደሙ ያሉት ባህላችንን፤ ወጋችንንና ቅርሶቻችንን ጨምር ነዉ እንዳልነበረ ያደረጉት። ለምሳሌ በብዙ የአለም አገሮች ዉስጥ ረጂም ዕድሜ ያስቆጠሩ ህንፃዎች፤ የታሪካዊ ሰዎች መኖሪያ ቤቶችና የተለያዪ የአገር ቅርሳቅርሶች ልዩ እንክብካቤ እየተደረገላቸዉ ከዘመን ወደ ዘመን እንዲተላለፉ የደረጋል። ኢትዮጵያ ወስጥ ግን ዕድሜ ለወያኔ ከፍተና ታሪካዊ እሴት ያላቸዉ ህንፃዎች በልማት ስም እንዲፈርሱ ይደረጋል። የጀግኖችን አጽም ያረፈበት የመቃብር ቦታም በግሬደር እየተደረመሰ የንግድና የችርቻሮ ቦታ ይሆናል።
ሌለዉ ወያኔ በታሪካችን ላይ የሚያደርሰዉ ጥፋት ታሪካችንን እንዳንማርና የታሪክ ተማራማሪዎቻችን በጥንታዊ ታሪካችን ላይ ምርምር እንዳያደርጉ እጅና እግራቸዉን ማሰሩ ነዉ። ለምሳሌ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ የሚገኛዉ የታሪክ ዲፓርትመንት የኢትዮጵያን ታሪክ ማስተማር ብቻ ሳይሆን ታሪካችንን ከተለያየ አቅጣጫ በማጥናትና ምርምር በማድረግ ለታሪካችን መበልጸግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ተቋም ነዉ። ሆኖም ይህ በተለያዪ መንግስታት ዉስጥ ለረጂም አመታት ትልቅ ስራ ሲሰራ የቆየዉ የታሪክ ዲፓርትመንት ዛሬ አለ ተብሎ መናገር በማይቻልበት አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ይህ ሁሉ የሚያሳየን ወያኔ የቀድሞ ታሪካችንን እያወደመ የሚቀጥለዉን ታሪካችንን ደግሞ በራሱ አቅጣጫ እያጣመመ በመጻፍ ላይ መሆኑን ነዉ።
ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች የኢትዮጵያን ታሪክ አስመልክቶ በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ታሪክ የተጻፈዉ በተወሰኑ ሰዎች ከአንድ አቅጣጫ ብቻ ነዉ ሲሉ በሌላ በኩል ደግሞ የረጂሙን ዘመን የአገራችን የኢትዮጵያ ታሪክ ከአንድ ሞቶ አመታ የበለጠ ዕድሜ የለዉም እያሉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ዛሬ በገፍ ለጨረታ ያቀረቧቸዉ የታሪክ መጽሐፍት ቁልጭ አድርገዉ የሚናገሩት ደግሞ ታሪካችን ከ3000 ሺ አመታት በላይ መሆኑንና የተጻፈዉም በተወሰኑ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በተለያዪ ኢትዮጵያዉያንና የዉጭ አገር ሰዎች ጭምር መሆኑንደ ነዉ። ዛሬ ወያኔ እንደ ርካሽ ዕቃ እያወጣ የሚቸበችባቸዉ መጽሀፍት ለዚህ አሳዛኝ ዕጣ የበቁት ይህንን የወያኔ አይን ያወጣ ዉሸት ስለሚያጋልጡ ነዉ።
አገራችን ኢትዮጵያን እንወዳለን የምንል ኢትዮጵያዉያን በሙሉ ይህ በአፋችን ሁሌም የምንለዉ ቃል በተግባር የምንተረጉምበት አጋጣሚ ፊት ለፊታችን ላይ ተደቅኗል። ኢትዮጵያ አንደ ገና ዳቦ ከላይና ከታች ወያኔ ባነደደዉ ረመጥ እሳት እየተለበለበች ነዉ። ይህንን እሳት ማጥፍትና አገራችንን ከወያኔ መታደግ ካለብን ግዜዉ ነገ ሳይሆን ዛሬ ነዉ።
አያሌ ኢትዮጵያዉያን የወያኔን የመጽሐፍ ሽያጭ አስመልክቶ የወሰዱትን ቆራጥና ብልህ እርምጃ ግንቦት ሰባት የፍትህ፤ የነጻነትና፤ የዲሞክራሲ ንቅናቄ እጅግ በጣም ያደንቃል። በአዲስ አበባና በአካባቢዋ የሚገኙ አያሌ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዉያን የአገርና የወገን ሃላፊነት ተሰምቷቸዉ ወያኔ ለጨረታ ያቀረበዉን መጽሐፍ በመግዛት የአገራቸዉን ታሪክ ለመታደግ ያደረጉት ጥረት በዋጋ ሊተመን የማይችል ትልቅ አገራዊ ስራ ነዉ። አገራችን ዛሬ ባለችበት ሁኔታ ነገ አትገኝም የሚል እምነታችን የጸና ነዉና እነዚህን የገዛችኋቸዉን መጽሀፍት በጥንቃቄ በመያዝ ሀላፊነትና የአገር አደራ ለሚሰማዉ በህዝብ የተመረጠ መንግስት አንድታስረክቡ አደራ እንላችኋለን። ከአሁን በኋላም ቢሆን የወያኔን ፀረ አገርና ፀረ ህዝብ ስራ እየተከታተላችሁ እንድታከሽፉና በሚያልፈዉ ህይወታችሁ የማያልፍ ታሪክ ሰርታችሁ ወያኔን በማሰወገዱ ዘመቻ ዉስጥ ሙሉ ተሳትፎ አንድታደርጉ አገራዊ ጥሪ እናስተላለፋለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

ESAT: Special Program, Free and Fair Election in Ethiopia Public Meeting in Seattle part 1 Nov 2014 | ESATTUBE

ESAT: Special Program, Free and Fair Election in Ethiopia Public Meeting in Seattle part 1 Nov 2014 | ESATTUBE