Tuesday, January 19, 2016

የነብርን ጭራ አይዙ ከያዙ አይለቁ!
እነሆ እኛ ኢትዮጵያዉያን ህብረት፣ መደጋገፍ፣ ስምምነትና አርቆ አሳቢነት የሚጠይቅበት ወሳኝ ወቅት ላይ ደርሰናል። ያለፉት ዓመታት የወያኔውን ጥቁር ሥርዓት ምንነት አሳይቶናል። ይህንን ብቻ አይደለም፤ በአምባገነን ሥርዓትና ለቅኝ ገዥዎች በባንዳነት በሚያድር ሥርዓት መካከል ያለውን ልዩነትም በሚገባ አሳውቆናል። የንጉሡ ዘመን ኋላ ቀር ነበር። የደርግ ዘመን አምባገነን ነበር። በሁለቱም ሥርዓት ወቅት ግን ሃገር ነበረች። ኢትዮጵያ እስከ ባህረ በሯ ሉዓላዊ እስከ ሕዝቦቿ ክቡር ነበረች። ዛሬ ለየት ያለ ነው። ወያኔ ዘረኛ ብቻ አይደለም። ወያኔ የሙስናዊ አምባገነን ሥራዓት ቋሚ ተጠሪ ስብስብ ተቋም ብቻ አይደለም። ወያኔ "የአናቁረህ ግዛ" ግፍ አራማጅ ብቸኛ የቀማኞች ድርጅት ብቻ አይደለም። ወያኔ ቅድስት ሃገር ኢትዮጵያን ለውጭ ባለሃብቶች የሸበሸበ የኃጢአተኞችና "የአስረሽ ምቺ" ዳንኪረኞች፣ መዝባሪዎች ስብስብ ብቻ አይደለም። ወያኔ የሁሉም የኃጢዓት ሥርዓቶች ድምር ነው። ወያኔ ድንገት ከተሰባሰበበት ደደቢት ሸለቆ ተንከባሉ ሠይጣን ዋሻ ውስጥ ለአመታት ከርሞ ዲያቢሎስ ሳያኝክ የተፋው የርኩስ ሥርዓት ቁንጮ ነው። እድሏ ሆኖ ቅድስት ኢትዮጵያ የዚህ ሥርዓት ተሸካሚ ሆናለች። እንዲያ እንዳልተከበረች፣ እንዲያ እንዳልተፈራች ሃገራችን ኢትዮጵያ ለቅኝ ገዥዎች ቅርጫ ቀረበች። ሥርዓቱ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን በቁሟ የገነዘ፣ ሕዝቧን ያስጨነቀ መሪር ሥርዓት ነው። ኢትዮጵያ ሃገራችንን ከዚህ ሥርዓት የሚገላግላት ቆራጥነትና በህብረት መነሳት ብቻ ነው። ህዝብን በመርዘኛ ራዕይ ሰልቦ፣ ወጣቱን በሥራ አጥነት አጠውልጎ ለስደትና ሴተኛ አዳሪነት እየዳረገ፣ ነዋሪውን በልማት ስምና በከተማ ማስፋፋት እያፈናቀለ ሕዝብን በቅኝ ገዥዎች ቋንቋና በምጣኔ ኃብት እድገት እያደናገረ የሃገሪቱን ሃብት መዝብሮ ወደ ውጭ በማሸሽና በከፍተኛ ዕዳ ውስጥ በመዝፈቅ በጥቂቶች ስም ሃብት እያከማቸ እስከ ዓለም ፍጻሜ ሊገዛ የሚቃጣ ዘመነኛ የግፍ ሥርዓት አራማጅ ወያኔ ብቻ ነው።
በዘረፉት ገንዘብ ልጆቻቸውን እንደ ልዑላውያን ልጆች በምዕራቡ ዓለም ወይም ቻይና በቅምጥል ሊያኖሩ የሚያስቡ ሞኞች ወቅቱን ያልተገነዘቡ ብቻ ናቸው። ከጭቁን ሕዝብ በተመዘበረ ነዋይ ኬክ ገዝቶ መዘመር፣ ሻምፓኝ አንስቶ ጤንነትን መመኘት ሲዖል አፋፍ ቆሞ ዲያቢሎስን መጋበዝ መሆኑን እንዲሆም ከረሃብተኞች በተነጠቀ ገንዘብ በተገዛ ሸማ መዋብ በደም በተለወሰ ክር የተሰፋ መሆኑ ገና ያልገባቸው ይልቁንም የሥርዓቱ መበስበስ ገና ያልታያቸው ርህራሄ ቢሶች ብቻ ናቸው። ከድሆች መሬት ነጥቆ በሙስና፣ በዘረፋ በተገነቡ ዘመናዊ ሕንፃ ውስጥ መኖር ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ መቀበር መሆኑ ገና ያልገባቸው እብሪተኞች ብቻ ናቸው። ከድሆች አፍ በተነጠቀ ገንዘብ ሠማይ ጠቀስ ፎቆቻቸውን ወደ ላይ አንጋጠው የሚመለከቱ የፀሃይ ብርሃን የማትጠልቅ የሚመስላቸው መሃይማን ብቻ ናቸው። ግንዛቤ ያጠራቸው ባለስልጣናትና ልጆቻቸው የሙስናው ተጠቃሚዎች፣ ገና በሼራተንና ሂልተን አልኮል የሚራጩት፣ የሉካንዳው ቤት ሠልፈኞች፣ የዳንኪራ ቤቱ ጋጠ ወጦችም ጭምር ሕዝባዊው ሱናሜ መምጣቱን ፈፅሞ ያልተገነዘቡት ዘመኖች ናቸው። እነርሱ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደሚፈነጥዙ ዓይነት የግፍ ሥሪቶች ናቸውና የገናናዋ ኢትዮጵያ እንባ ያቅበዘብዛቸዋል። የገባቸው፣ አዎ የገባቸው ገዥዎች፣ ነገ ዓይደለም ዛሬውኑ ራሳቸውን ነፃ ያወጣሉ። የገባቸው፣ የአምላክ ምህረት የቀረባቸው፣ ይቅርታ ጠይቀው መጪው ዘመን ለነሱም ለሃገሪቱም ብሩህ እንዲሆን ይተጋሉ። የገባቸው፣ ልባቸው ያልደነደነው የግፍ ሥርዓት ፈጽሞ እንዲቀበር የሚመኙ የሕዝቡን ጥያቄ ይቀበላሉ። የገባቸው፣ የድሆች እንባ ሲንቆረቆር አይተው ልባቸው በርኅራሄ የረሰረሰው አዲስ ታሪክ ይሠራሉ። ያዘኑ፣ የረሃብተኛውን ሕጻን አጥንት የቆጠሩ የነጠፉ ጡቶችን አይተው የሚያለቅሱ ገዥዎች ሥልጣናቸውን በሠላም ለህዝብ ያስረክባሉ። ዕድሉ አሁንም አለ። ይህ ዕድል ነገ ላይኖር ይችላል። ሳዳም ሁሴንና ጋዳፊ፣ ያውም ሃገራቸውን ከልብ የሚወዱት እንኳን ይህ ዕድል አምልጧቸዋል። እናንተስ?
ዛሬ የበደሉ ጽዋ ሞልቶ ቢፈስ ሕዝብ በቁጣ ተነስቷል። ሕዝብ በቃኝ፣ መረረኝ ብሏል። ሁሉም ሊተባበርና ከትግሉ ጎን መሰለፍ አለበት። ዛሬ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ አፋር፣ ትግራይ፣ ወላይታ፣ ሲዳማ፣ አኙዋክ፣ ከንባታ፣ ከፊቾ እያልን የገበጣ ጨዋታ የምንጫወትበት ወቅት አይደለም። እኛ ኢትዮጵያውያን እንደቀድሞ ተታለን አንድ የበሰበሰሰ ሥርዓት በሌላ አፋኝ ሥርዓት ሲተካ አይተን ዝም የምንል ወይንም ወያኔ አንዱን ዘር ካንዱ ሊያጋጭ በተለመው "የአልሞት ባይ ተጋዳይ" ስልቱ ውስጥ የምንዘፈቅለት ቂሎች አይደለንም። እኛ ኢትዮጵያውያን ትግሉን አመካኝቶ ሌላ ነውጥ ሊያመጣ የሚችል ኃይልን እሹሩሩ የምንልም አይደለንም። እኛ ኢትዮጵያውያን ከዚህ በኋላ ፈጽሞ አንከፋፈልም። የወያኔው ሥርዓት የጥቁር አምባገነንነትን ቀለም፣ የአንድ ዘር የበላይነት የቅኝ ገዥዎች ቅጅ የግፍ አገዛዝ መርህን፣ የእብለት አካሄድንና የሸፍጥ ስልት ፖለቲካ ምንነትን እንድናውቅ አስችሎናል። በእርግጥ ዘረኝነትንና ልዩነትን አሽቀንጥረን በኅብረት እንድንታገል፣ በአንድ ላይ እንድንቆምም ትምህርት ሆኖናል። በልማት ስም ቅኝ አገዛዝዝን በዲሞክራሲ ስም ጭለማ ያመጣብንን ሥርዓት ሁላችንም መርምረነዋል። እነሆ ዛሬ - ሁላችንም በአንድነት "መሬት ላራሹና" "ሕዝባዊ መንግሥት" ይመስረት መፈክሮችን የምንተገብርበት ወሳኝ ዘመን ላይ ደረስናል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከዳር እስከ ዳር በአንድነት ተነስቷል። ዛሬ የተጀመረው ሕዝባዊ ትግል ቢዳከም እንደገና መቀመቅ ውስጥ የምንገባው እኛው ነንና ትግሉን ይበልጥ ማፋፋም አለብን። "የነብርን ጭራ አይዙ - ከያዙ አይለቁ!
ሕዝብ ያሸንፋል፤ ኢትዮጵያ እንደቀድሞዋ በነጻነትዋ ትራመዳለች። ኢትዮጵያ ግርማ ሞገሥዋ ይመለሳል።
ሚክያስ ግዛው

Thursday, December 24, 2015

የመስመር ልዩነት የሌላቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች በቶሎ ወደ አንድነቱ
መምጣት አለባቸው። ለሃገሪቱ ርጥብ ራዕይ ያላቸው ድርጅቶች ሁሉ መቀራረብ አለባቸው። ኢትዮጵያ
የምታገግመው ከትግሉ ሜዳ በተለያዩ ምክንያት የራቁትን ጀግኖቿን በፍቅር ተማጽኖ ትግሉን እንደገና
እንዲቀላቀሉ ሲደረግ ነው። ማዕከላችን ኢትዮጵያ ነች። ሁላችንም ለኢትዮጵያ እናስባለን። ልዩነታችን
ውበታችን ነው። አንድነታችን አምባገነንነትን ያንበረክካል። ሙስናን ያጠፋል። ኢትዮጵያ የሰው ልጆች መብት
የማይረገጥባት ሀገር ትሆናለች።

አምላክ ኢትዮጵያን ይጠብቃት።




Friday, December 18, 2015

How Corrupt Is Ethiopia?

ትግላችንን ተጠናክሮ በአንድነት ይቀጥል!

December 17, 2015
def-thumbየኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱ በያቅጣጫው መነሳቱ የሚያኮራ ነው። ባለፉት 3 ዓመታት ብቻ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ያደረጉትን የመብት ትግል ጨምሮ በደቡብ፣ አማራ፣ አፋር፣ ጋምቤላና በሌሎችም አካባቢዎች በርካታ የነጻነት ትግሎች ተካሂደዋል። አሁን በኦሮምያ እና በአማራ በተለይም በሰሜን ጎንደር አካባቢዎች እየተካሄዱ ያሉት የነጻነት ትግሎች የአጠቃላዩ የነጻነት ትግል አካሎች ናቸው። በእነዚህ የነጻነት ትግሎች ገዢው ፓርቲ ከህዝብ ጋር ለምንጊዜውም መለያየቱን ለማየት ችለናል። ስልጣኑን ለማስጠበቅ ሲልም፣ አቅሙ ቢፈቅድለትና ማግኘት ቢችል በምድር ላይ ያሉትን ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን ሁሉ በገዛ ህዝቡ ላይ ለመጠቀም ወደ ሁዋላ የማይል የአረመኔዎች ስብስብ መሆኑን አረጋግጠናል። በጭካኔውና በፍርሃቱ ብዛት የተነሳ በርካታ ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች፣ መብታቸውን በሰላም ለመጠየቅ ወደ አደባባይ የወጡ ወጣቶች ተገድለዋል፤ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ጋዜጠኞች በእስር ተንገላተዋል፤ በእስር ቤትም ማንነታቸውን ከማዋረድ ጀምሮ የተለያዩ አካላዊ ጥቃቶች ተፈጽሞባቸዋል።
የኦሮሞ ህዝብ መብቴ ይከበርልኝ ብሎ መነሳቱን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ከያቅጣጫው ድጋፋቸውን እየገለጹ ነው። ይህ ለነጻነት ሃይሎች ብስራት ሲሆን ዘርን ከዘር በማጋጨት የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ለሚፈልገው የሽፍታ አገዛዝ ደግሞ ትልቅ መርዶ ነው። ባለፉት 25 ዓመታት ወያኔ አንዱን ዘር ከሌላው ዘር እያጋጨ፣ በወንድማማቾችና እህትማማቾች መካከል መተማመን እንዳይፈጥር መርዙን ሲረጭ ቆይቷል፤ ያሰበው አልሰምርለት ሲል ደግሞ በአገሪቱ አንጡራ ሃብት በሸመተው ጠመንጃ ለመብቱ የተነሳውን ህዝብ ደረት ደረቱን እየመታ ፈጅቶታል። በተለይም የአማራው ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በአንድነት ተሰልፎ በህወሃት አገዛዝ ላይ የነጻነት ክንዱን ለማሳረፍ እንዳይችል ሌት ተቀን የጥላቻ መርዙን በመርጨት ከሌላው ህዝብ ጋር እንዲጋጭ ለማድረግ በእጅጉ ደክሟል። ወያኔ የረጨውን የጥላቻ መርዝ የኦሮሞ እና የአማራ ልጆች በጋራ እያረከሱት መገኘታቸው፣ የሌሎች ብሄሮችና ብሄረሰቦች ህዝቦችም እንዲሁ ” አንለያይም” በማለት በጋራ ለመሰለፍና ትግሉን ለማቀጣጠል ዝግጁነታቸውን መግለጻቸውና በተግባር እያሳዩ መምጣታቸው የ25 አመታት የወያኔ የአፈናና የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ እያከተመ መምጣቱን የሚያመላክት ነው። ወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው በመላው ኢትዮጵያውያን ትብብር እንደረከሰበት ሲያውቅ ደግሞ የግድያ አዋጅ አውጥቶ በ-ኢትዮጵያውያኑ ላይ ጥይት አርከፍክፎ ጸጥ ሊያሰኛው መዘጋጀቱን በአዋጅ አስነግሯል። ከታሪክ መማር የማይችለው ጠባቡ ወያኔ፣ ህዝባቸውን አዋጅ አስነግረው የገደሉ ጨቋኝ መንግስታት መጨረሻቸው ምን እንደነበረ እንኳን ቆም ብሎ ማሰብ አልቻለም። ዛሬ የእሳት ላንቃ በሚተፋ ጠመንጃቸው ሊጨፈልቀው የሚያስበው ህዝብ ነገ መልሶ ራሱን እንደሚጨፈልቀው ለአፍታም ቢሆን ለማሰላሰል አልቻለም። የዘረፈው ሃብትና የታጠቀው መሳሪያ አእምሮውን ደፍኖት፣ እየመጣ ያለውን ህዝባዊ ሱናሚ ለማየት ተስኖታል። በጦር መሳሪያ ጋጋታና ድንፋታ ቢሆን ኖሮ ወራሪዋ ጣሊያን እስከዛሬ ድረስ ከአገራችን ለቃ ባልወጣች ነበር፣ በጦር መሳሪያ ጋጋታ ቢሆን ኖሮ እነ ጋዳፊን ዛሬ ቤተመንግስት እንጅ መቃብር ውስጥ አናገኛቸውም ነበር።
የአገራችን ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለነጻነቱ የሚያደርገውን ትግል በጥንቃቄ የሚመራበት ጊዜ ላይ ነን ። የገጠመን ጠላት በታሪካችን አይተነው የማናውቅ፣ የገዛ ህዝቡን በጠላትነት ፈርጆ ሊያጠፋው የተነሳ በመሆኑ፣ አገዛዙ እስከዛሬ ካደረሰው ጥፋት ሌላ ተጨማሪ ጥፋት ሳያጠፋ፣ ከአገራችን መሬት ለመንቀል እንድንችል እርምጃችን ሁሉ ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን ይገባል። ጠላታችን ህዝብን ከህዝብ ለማፋጀት ያለ የሌለ ሃይሉን የሚጠቀም መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ አቅሙ በፈቀደለት መጠን ሁሉ ህዝቡን በጅምላ ለመፍጀት ወደ ሁዋላ የማይል ነው። ህዝቡ የጠላቱን አውሬነት ተገንዝቦ እሱ በሚከፍተው ቀዳዳ ዘው ብሎ ላለመግባት መጠንቀቅ አለበት። ሊገድሉን ሲመጡ ዘወር ብሎ በማሳለፍ፣ እንደገና ደግሞ ወደ አደባባይ በመውጣት፣ እንዲሁም የተቃውሞውን አድማስ በማስፋትና የሃይል መከፋፈል እንዲፈጠር በማድረግ ወያኔን አዳክሞና ተስፋ አስቆርጦ ካለሙት ግብ መድረስ ይቻላል። አሁን እየታየ ያለው አንድነት ይበልጥ እየተጠናከረ፣ ከኦሮሞው ጎን አማራው፣ ከአማራው ጎን ጉራጌው፣ ከጉራጌው ጎን ትግሬው፣ ከትግሬው ጎን አፋሩ፣ ከአፋሩ ጎን ጋምቤላው፣ ከጋምቤላው ጎን ሀረሪው፣ ከሃረሪው ጎን ጉሙዙ፣ ከጉሙዙ ጎን አዲስ አበቤው፣ ከአዲስ አበቤው ጎን ጋሞው በአጠቃላይ መላው ህዝብ እጅ ለእጅ እየተያያዘ የነጻነት ባበሩ ወደፊት እንዲሮጥ ማድረግ አለበት። ወጣቱ ራሱን ባለበት ቦታ እያደራጀና አመራር እየሰጠ በያቅጣጫው የጀመረውን የነጻነት ትግል አጠናክሮ ይቀጥል።
አርበኞች ግንቦት7 ትግሉን በተለያዩ አቅጣጫዎች አጠናክሮ ቀጥሎአል፤ የአርበኛው ሰራዊት የወያኔን ጀሌዎች በቀኝና በግራ መውጫና መግቢያ እያሳጣቸው ነው። የንቅናቄው አባላት በዳር አገር በአፈሙዝ፣ በመሃል አገር ደግሞ ወጣቱን እያደራጁ ለትግል እንዲሰልፍ እያደረጉት ነው። የንቅናቄያችን መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ “ከነጻነት ትግሎች ጎን አለን” እንዳሉት የአርበኛው ልጆች ፊት ለፊት ተሰልፈው አመራር በመስጠት የነጻነት ትግሉን ለማቀጣጠል እና መከፈል ያለበትን የህይወት መስዋትነት ለመክፈል ተዘጋጅተው በያቅጣጫው እየተንቀሳቀሱ ነው።
ተደጋግሞ እንደተነገረው የአርበኞች ግንቦት7 አላማ በአገራችን የዲሞክራሲያዊ የሽግግር ስርዓት ማስጀመር ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዚህ አላማ ዙሪያ ተሰልፎ ትግሉን ይቀጥል። ይህን አላማ የሚደግፉ የፖለቲካ ድርጅቶችም ዛሬውኑ ከጎናችን ተሰልፈው ወያኔን ለማስወገድ በሚደረገው የሞት ሽረት ትግል ይሰለፉ!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
አገራችን በልጆቿ ነጻ ትወጣለች!
አርበኞች ግንቦት7

ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍበ ኖርዌ ኦስሎ ከተማ ተደረገ

በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን የወያኔ መንግስት በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ ያደረሰውን ኢሰብአዊ ግድያ እና በምዕራብ ኢትዮጵይ በጎንደር ክልል ለሱዳን ተላልፎ የሚሠጠውን መሬት ምክንያት በመቃወም ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍበ ኖርዌ ኦስሎ ከተማ ተደረገ።

Wednesday, December 16, 2015

ልብ በሉ፦

ልብ በሉ፦ ወያኔን ማስወገድ ያለብን የቅኝ ገዢዎች ተባባሪዎች፣ ለሀገሪቱ ሉዓላዊነት፣ ክብርና ታሪክ
ፈጽሞ የማይጨነቁ፣ ሃገሪቱን ወደብ አልባ ያደረጉ፣ ኃይማኖትን የበከሉ፣ ሕዝቡን ለስደት ሞትዕና ለዳግም
ክፉ ቀን የዳረጉ ሰው መሰል ጨካኝ አራዊቶች ስለሆኑ ነው። ይህ ደግሞ በኢንተርኔት፣ ፓልቶክ፣ ሬድዮና
ቴሌቪዥን በሚተላለፍ ትግልዕ ብቻ አይሞከርም። ዛሬ በአቶ መለስ የሙት መንፈስ ምስል እየተመራ
በመበታተኑ ጣዕረ ሞት የሚያቃስተውን ወያኔን ገፍትረን መጣል ካልቻልን ነገ አገግሞ ለሌላ መቅሰፍት
ይዳርገናል።
አምላክ ኢትዮጵያን ይጠብቃት።