Monday, January 20, 2014

Hello, world!
 | 

በደምና በአጥንት መስዋዕትነት ተከብሮ የቆየ የሃገራችንን ዳር ድንበር ለባዕድ አሳልፈን አንሰጥም!

By BERHANE ASSEBE
Dccc
ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ የታደለች ፣መልካም የአየር ፀባይ ያላት፣ህዝቦቿ የራሳችን አኩሪባህልና ወግያለን፣የራሳችን መልካም መልክዓ ምድራዊና አሰፋፈር ያለን በጋራ ተሳስረን አብረን የኖርንባትና የምንኖርባት በየትኛውም ዘመን ሉአላዊነቷ ያልተደፈረ ለአፍሪካ ተምሳሌት የሆነች ሀገር ናት። በተለያየ ወቅት የተፈጥሮ ሃብቷን ለመቀራመትና ሉአላዊነቷን ለመዳፈር የሞከሩ ሃገራት ሁሉ፣በውድ ልጆቿ የተባበረ ክንድ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥተው ኢትዮጵያን ዳግም እንዳይመኟት የተባረሩበትና የኢትዮጵያን አይበገሬነት በአፍሪካም ሆነ በአለም መድረክ ያስመሰከረች፣ አንድነቷንና ሉዓላዊነቷን ጠብቃ በማቆየት በአለም ታሪካዊ ስፍራ ያላት፣ በቀደምት ውድ ልጆቿ የደም መስዋዕትነት ሀገራችን ሉአላዊነቷ ሳይደፈር ለብዙ ሺ አመታት ቆይታለች።
በአሁኑ ስዓት ኢህአዴግ/ህወሃት ለግልና ለግዚያዊ የፖለቲካ ጥቅም ሲል የኢትዮጵያን አንድነት በማደብዘዝ እንሆ በእኛ ዘመን ለዘመናትተደፍሮ የማያውቀውን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በመጋፋት የኢትዮጵያ የሉአላዊነት ባለቤት የሆኑት ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሳይወያዩበትና ሳያፀድቁት በጓሮ በር የኢትዮጵያን መሬት ለባዕድ ሃገር/ሱዳን ቆርሶ ለመስጠት ሽርጉዱን ተያይዞታል። ከአመታት በፊት በምዕራቡ የሃገራችን ክፍል /ድንበር በኩል/ በመሸራረፍ ለም የሰሊጥ ምርት የሚሰጥ መሬት ለሱዳን ሲሰጥ ዝም በማለታችን እንሆ ዛሬ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጋፋ ፣ የኢትዮጵያን ቅርጽ የሚያጠፋ ረጅም ርዝመት ያለው ለም መሬት ለሱዳን ለመስጠት ዝግጅቱ መጠናቀቁን ሰማን ።
ዛሬ ላይ ሆነን ይህንን መሰሪ ተግባር አንድነታችንን አጠናክረን መግታት ካልቻልን ነገ ደግሞ በሌላኛው የኢትዮጵያ ጫፍ በኩል የኢትዮጵያ መሬትተቆርሶ ለሌሎች አጎራባች ሀገራት ላይሰጥ ምን ዋስትና አለን ?
አያቶቻችንና አባቶቻችን ደማቸውን ገብረው ፣አጥንታቸውን ከስክሰው ያስረከቡንን የሀገር ሉአላዊነት ሳይሸራረፍ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ የእኛ የአሁኑ ትውልድ የታሪክ ግዴታ ነው። ይህን የታሪክ ግዴታችንን ሳንወጣ/ችል በማለት/ በመሰሪው የህወሃት/ ኢህአዴግ አመራር የሃገራችን ሉአላዊነት እየተሸራረፈ ለባዕድ ሀገራት ሲሰጥ በምን አገባኝ ስሜትዝም ብለን ብንመለከት በ– ዚ–ያ ዘመን ዘመናዊ መሳሪያ ከታጠቀ የውጭ ጠላትጋር የሀገሬን ሉአላዊነት አላስደፍርም በማለት በዱላ፣ በጦርና ጋሻ፣ ዘመናዊ ባልሆነ የጦር መሳሪያ ፣በባዶ እግራቸው በመዝመት ደማቸውን አፍስሰው ፣ አጥንታቸውን ከስክሰው የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ሳያስደፍሩ ያስረከቡን የአባቶቻችን አጥንት እሾህ ሆኖ ይወጋናል።
«የኢትዮጵያ ድንበሮች በኢትዮጵያውያን ደም የራሱ፣ በኢትዮጵያውያን አጥንት የተገነቡ ሲሆኑ ድንበሮቻችንን ለማስከበር ከሁልቆ መሣፍርት፣ ተራ ዜጐች አንስቶ እስከ አንድ ታላቅ ንጉሠ ነገሥት አጼ ዮሐንስ አንገታቸው ሰጥተዋል፡፡ በዶጋሊ፣ በጉራዓ፣ በጉንዲት፣ በመተማ፣ በአድዋ፣ በወልወል በቅርብ ጊዜያት ደግሞ በሶማሊያና በኤርትራ የፈሰሰው የኢትዮጵያውያን ደም የሌላውን ግዛት በመቋመጥ ሳይሆን ድንበሬን አላስነካም በሚል ነበር፡፡ እንደዛሬው መኪና ወይንም ባቡር ባልኖረበት የቀደምት ኢትዮጵያውያን ከመሃል አገር ተነስተው በእግር ለወራት በረሃውን አቋርጠው፣ ተራራውን ወጥተው፣ ንዳዱን ተቋቁመው፣ ወባውን ደፍረው ከሙስታሂል እስከ ጋምቤላ፣ ከራስ ካሣር እስከ ሞያሌ ዘልቀው ድንበሩን ሰፍረው ኢትዮጵያን ለዚህ ትውልድ አስረክበው ሄዱ፡፡ ይህ ተረካቢ ትውልድ የተረከበውን መሬት ሳይቀነስ ለቀጣዩ ትውልድ ያስተላልፋል ይሆን—-«ከያዕቆብ ኃይለማሪያም/20 July 2008/።
ይህ ትውልድ ከአባቶቹ የወረሰውን አደራ ጠብቆ የሀገሩን ሉአላዊነት ሳይሸራረፍ በማስከበር ለመጭው ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ ያለበት መሆኑን ለአፍታ መዘንጋት የለበትም ። ህወሃት/ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ ህዝብ እውቅና ውጭ በሚስጥር የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በመጋፋት ዳር ድንበራችንን ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት የተደረገውን የውል ስምምነት የፖለቲካ ልዩነት፣ ብሄር፣ ሃይማኖት፣አመለካከት ሳይለያየን የፖለቲካፓርቲዎች ፣ ድርጅቶች፣ ሲቪክስማህበራትና ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በጋራ ተንቀሳቅሰን አሁኑኑ ማስቆም ካልቻልን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ከማስደፈርም አልፎ እስከ ወዳኛው ትውልድ ድረስ ብጥብጥና ትርምስን የሚያወርስ ስውር ደባ ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉአላዊነት በመጋፋት ለም መሬታችንን ለሱዳን አሳልፎ የሚሰጠውን ስምምነት አገር ወዳድ የሆንን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በጋራ በመንቀሳቀስ በደምና በአጥንት መስዋዕትነት ተከብሮ የቆየ የሃገራችንን ዳር ድንበር ለባዕድ አሳልፈን አንሰጥም! በሚል መርህ ተግባብተን ይህንን እኩይ ተግባር ለማስቆም ግዜ ሳንወስድ በያለንበት ፈጥነን መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል።
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለባዕድ ሀገር አሳልፎ የመስጠት ታሪክ አልወረስንም!

“የአፄ ምኒልክ ወታደሮች በአያቴ ላይ ብዙ በደል አድርሰዋል” – ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (ቃለምልልስ) | Zehabesha Amharic

“የአፄ ምኒልክ ወታደሮች በአያቴ ላይ ብዙ በደል አድርሰዋል” – ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (ቃለምልልስ) | Zehabesha Amharic

Hiber Radio: “እነ ሌንጮ ሰልፋቸውን እስከምናውቅ አቋም አልያዝንም” ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ አቶ ቡልቻም ስለ ሌንጮ ይናገራሉ | Zehabesha Amharic

Hiber Radio: “እነ ሌንጮ ሰልፋቸውን እስከምናውቅ አቋም አልያዝንም” ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ አቶ ቡልቻም ስለ ሌንጮ ይናገራሉ | Zehabesha Amharic

Thursday, January 9, 2014

ቴዲ አፍሮና የቢራው ፖለቲካ (ክንፉ አሰፋ)

ቴዲ አፍሮና የቢራው ፖለቲካ

(ክንፉ አሰፋ)
teddyafro
በጋዜጠኛ ስህተት የወጣች አንዲት ጽሁፍ ምክንያት 18 ሺህ ፊርማ በኢንተርኔት መሰበሰቡን ሰማን። ጽሁፉን ያሳተመው መጽሄት ስህተቱን አረመ። ይቅርታም ጠየቀ። ዘመቻው ግን እንደቀጠለ ነው። ቴዲ አፍሮ ይንን እንዳልተናገረ መግለጫ ቢሰጥም ጉዳዩ እልባት ሊያገኝ አልቻለም።   ከቶውንም አንድነታችንን የማይፈልጉ ምእራባውያን ጭምር ይህችን ምክንያት በመያዝ ጉዳዩን ማረገብ ጀመሩ። አንድ የዳች ጋዜጣ አጼ ምኒሊክን ከሂትለር ጋር አመሳስሎ በመጻፍ ጋዜጣውን በዚህ ሳምንት አሰራጭቷል! ያለ አንዳች መረጃ። “ለነጮች እጄን አልሰጥም!” ብሎ አድዋ ላይ ስላዋረዳቸው ምኒሊክን ለማንቋሸሽ ምንም መረጃ አያስፈልጋቸውም።
እልፍነሽ ቀኖ የተባለች የኦሮምኛ ሙዚቃ አቀንቃኝ በአንድ ወቅት በለቀቀችው ነጠላ ዜማ ምክንያት ማእከላዊ እስር ቤት ታስራ ነበር። ምርመራውን የሚያካሂዱት ሰዎች በመጀመርያ የዘፈኑ ግጥም ወደ አማርኛ እንዲተረጎም አደረጉ። በግጥሙ ምንም አይነት የወንጀል ነገር ሲያጡ ግጥሙ “የህግ ትርጉም ይደረግለት” ሲሉ አዘዙ። የህግ ትርጉሙም ብዙ ስላላስኬዳቸው ለግጥሙ የፖለቲካ ትርጉም እንዲሰጠው አደረጉና ሙዚቀኛዋን “ጥፋተኛ ነሽ” ሲሉ ከሰሱ።  የፖለቲካ ትርጉሙ “ይህን ያለችው እንዲህ ለማለት ነው…”  ከማለት ተነስቶ አቀንቃኝዋ በልቧ አስባው ይሆናል የሚለውንም ያካተተ ነበር። በኢትዮጵያ “የፍትህ ሰዎች” የምናስበውንም ያውቁ ኖሯል።
የበደሌ ቢራ አድማ ጠሪዎች ቴዲ አፍሮ በልቡ ያሰበውን የማንበብ ሃይል እንዳላቸው አናውቅም። እሱ ግን የተባለውን ነገር እንዳልተናገረ ገልጾላቸዋል።
አጼ ምኒሊክ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ያከሄዱት ጦርነት “ቅዱስ ጦርነት ነው” ወይንም “አይደለም” የሚለውን ሙግት ለግዜው ወደጎን እንተወው። ምክንያቱም የዚህ ውይይት ውጤጥ የኦሮሞ ህዝብ አሁን ላለበት ችግር የሚፈይደው አንዳች ነገር የለም። የህሊና አይኖቹን ክፍት አድርጎ ለሚመለከት ሁሉ፤ የዛሬው የኦሮሞ ህዝብ ችግር የበዴሌ ቢራን ከመጠጣት እና ካለመጠጣት የላቀ ነው። ለነገሩ እንጂ 90 በመቶ የሚሆነው የኦሮሞ ህዝብ የሚተዳደረው በግብርና፤ ኑሮውም ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ የበደሌ ቢራን የመጠጣት አቅሙም ሆነ እድሉ የለውም። የዚህ ዘመቻ መሪ ተዋንያን የሆነው ጃዋር መሃመድ እንደነገረን ከሆነ ደግሞ 90 በመቶው የኦሮሞ ህዝብ የሙስሊም እምነት ተከታይ ነው። በሙስሊም አልኮል “ሃራም” ነው።
jawar“እስር ቤቱ ሁሉ ኦሮምኛን ይናገራል!” ያለው ማን ነበር? አዎ! የስርዓቱ ቁንጮ የነበረው ስዬ አብርሃ ነው። ስዬ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ከርቸሌ ታስረን የነበርን ጋዜጠኞች የእነ ኦቦ ባይራን ጉዳይ እያነሳን በኦነግ ስም በግፍ ለታሰሩት ስንጮህ የዝሆን ጆሮ ነበር የሰጠን።  አቶ ስዬ አብርሃ አይኑ የተከፈተውና ጆሮው ኦሮምኛን መስማት የጀመረው እጆቹ  የኋሊት ታስረው ቃሊቲ ሲወርድ ነበር። በእርግጥ ማየት ማመን ነው። ያየውንና የሰማውን በመመስከሩ ሊመሰገን ይገባዋል። ልብ በሉ። እስረኛው ሳይሆን እስር ቤቱ ነው ኦሮምኛ እየተናገረ ያለው።
ሂዩማን ራይትስ ዋች ሰሞኑን በለቀቀው ዘገባ፤ በኦሮሞ ወገናችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን አስከፊ ስቃይ በድምጽና በምስል ጭምር አሰራጭቷል። ይህንን ስቃይ ለማስቆም የፌስቡክ ታጋዮቹ ስንት ሺህ ፊርማ እንዳሰባሰቡ አልነገሩንም። የበዴሌ ቢራን የኦሮሞ ህዝብ እንዳይጠጣ በ24 ሰዓታት ውስጥ 18 ሺ ፊርማ ተሰብስቧል ብለውናል።
እርግጥ ነው። “ሰብአዊ መብት ይከበር!” የሚል ዘመቻ ከመጀመር ይልቅ “ቢራ አትጠጡ!” ማለቱ ቀላል ሊሆን ይችላል።  በምእራቡ አለም የሚመረተውን ሄነከን ቢራ ራሳቸው እየተጎነጩ  ይህንን ቀጭን ትእዛዝ ሲያስተላልፉ ግን በዚያ ትልቅ ህዝብ ላይ እያሾፉበት መሆኑን የዘነጉት ይመስላል።
የኦሮሞ ልሂቃን ግራ ያጋቡኛል። ይህን ስል ያለምክንያት አይደለም።  በአባ ጅፋር ግዛት ተወልጄ በኦሮሞ ባህል ታንጼ ነው ያደግኩት።  በደሙ ብቻ ‘ኦሮሞ ነኝ’  እያለ ከሚመጻደቀው ይልቅ የኦሮሞን ህዝብ ማንነት ጠንቅቄ አውቀዋለሁ። ቋንቋው፣ ባህሉና ስነልቦናው ውስጡ ሰርጎ ሳይገባ በደሙ ብቻ ራሱን እየለካ ከህልም እና ከቅዠት አለም ውስጥ ገብቶ የኋሊት ከሚራመደው በተሻለ መንገድ።  . . . እናም አንድ የኦሮሞ ህዝብ አውቃለሁ።  በቋንቋው፣ በባህሉና በታሪኩ የሚኮራ ህዝብ። ታታሪና ሰራተኛ ህዝብ። ከሌላው ጋር ተዋልዶና ተከባብሮ በፍቅር አብሮ የሚኖር ህዝብ።   የኦሮሞ ህዝብ  ከሌላው ወገኑ ጋር በደም ተሳስሯል። ሃቁ ይህ ነው። ግና ፖለቲከኞቹ ከዚህ ህዝብ በሁለት ሺህ ማይልስ ርቀው በምእራቡ አለም በሚሰሩት ስራ ይህንን ትልቅ ህዝብ እጅግ ትንሽ የሚያደርግ መሆኑን ያስተዋሉት አይመስለኝም።
በቅርቡ ሳውዲ አረቢያ በወገኖቻችን ላይ የፈጸመችውን ግፍ ለመቃወም በአለም ዙርያ ያለ ኢትዮጵያዊ በጋራ በሚጮህበት ወቅት አንድ እንግዳ ክስተት በኢንተርኔት ላይ ወጥቶ አየን። “ሳውዲ አረቢያ ኦሮሞን አትግደሉ፣ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ አይደለም፣ ኦሮሞ ወንጀለኛ አይደለም።” የሚል መፈክር የሚያሰሙ ሰዎች ለብቻቸው ሰልፍ ወጡ። እነዚህ ሰዎች የተሰለፉት “ኦሮሞን አትንኩ። ሌሎቹ ግን ወንጀለኞች ስለሆኑ ይገባቸዋል” የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ነበር።  መቼም ከማንም ሰብአዊ ፍጡር እንዲህ አይነት ኢ-ሰብአዊ አባባል አይጠበቅም። ድርጊታቸው ያሳፍራል። አንገትም ያስደፋል። ይህ አሳፋሪ ድርጊት እኔን እንዲህ ካሸማቀቀኝ፤  አፈር ስንፈጭ ያደግነው በኢትዮጵያዊነታቸው የሚኮሮ የኦሮሞ ልጆች ቢያዩት ምን ሊሉ እንደሚችሉ በምናቤ እስል ነበር።  በዚያ ትልቅ ሕዝብ ስም አደባባይ ወጥተው፣ ተግባራቸው ግን ማስተዋል የተሳነው ትንሽ ህዝብ ነበር።  ያንን ኩሩ ህዝብ እንዲህ … እንዲህ እያሉ ሊያሳንሱት አየን።
እ.ኤ.አ. በ1998 ገደማ አቶ ዳዊት ዮሃንስ በሆላንድ ውስጥ ህዝባዊ ስብሰባ ጠርቶ ነበር። ከስብሰባው መሃል አንድ ሰው ከመቅጽበት ተነስቶ ”ለኦቦ ነጋሶ ጊዳዳ የሚያደርሱልኝ ጥብቅ መልእክት አለኝ”  አለ። ስብሰባውን የሚመራው አቶ ዳዊት ዮሃንስም ሰውዬው ተነስቶ መልእክቱን እንዲናገር ፈቀደለት። ሰውየው ከመቀመጫው ተነሳ።
“ፊንፊኔ መሃል ላይ ያለው የምኒሊክ ሃውልት በአስቸኳይ እንዲነሳ ይንገሩልን!” አለ ፊቱን ቅጭም አድርጎ በኩራት እየተናገረ።  በስብሰባው የነበርን ሰዎች ግን ለተናጋሪው አፈርን። ያሳፈረን ይህንን መልእክት ማስተላለፉ አልነበረም። ሰውየው ሊናገር ከመቀመጫው ሲነሳ ሌላ አንገብጋቢ ጉዳይ ያነሳል ብለን ገምተን ስለነበር እንጂ።  ”ሰዎች በዘራቸው (በኦሮሞንታቸው) ብቻ የሚታሰሩት፣ የሚሰቃዩትና የሚገደሉት እስከመቼ ነው?” የሚል መልእክት ነበር የጠበቅነው። ምክንያቱም ወቅቱ በቁጥር 20 ሺህ የሚደርስ የኦሮሞ ተወላጆች የጦር ካምፕ እስረኛ እንዲሆን ካደረጉ በኋላ፤ የኦነግ መሪዎች በባሌ ሳይሆን በቦሌ እየተሸኙ የወጡበት ሰሞን ነበር።  የኦነግ መሪዎች ከህወሃት ጋር በጋራ መስርተውት የነበረውን ቻርተር ረግጠው በመውጣታቸው ምክንያት ኦሮሞው ወገናችን የህይወት መስዋእትነት ጭምር ይከፍል የነበረበት ወቅት።teddy menelik
ዳዊት ዮሃንስም አግባብ ያለው ጥያቄ መሆኑን ከተናገረ በኋላ መልእክቱን ለርእሰ-ብሄሩ እንደሚያደርስ ቃል ገብቶ ሄደ።  መልእክቱን ለዶ/ር ነጋሶ ያድርስ፤ አያድርስ የታወቀ ነገር የለም። ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በዚያን ወቅት የሃገሪቱ ርዕሰ-ብሄር ነበሩ። እንኳንና የተባለውን መልእክት ሊያስፈጽሙ፤  እሳቸውም የዛ ስርዓት ሰለባ ሆነው አየን።
የተዛባ ታሪክ ይዘን፣  ጥላቻን ብቻ በምናባችን አርግዘን የት እንደምንደርስ አላውቅም። አሁንም በመፍትሄው ላይ ሳይሆን በችግሮቹ ላይ ተወጥረናል።  የምኒሊክ ሃውልት ተነሳም አልተነሳ እንደ እንስሳ ለሚታደነው የኦሮሞ ህዝብ ምን ፋይዳ አለው?  “በእስር ያሉ ወገኖቼ ይፈቱ!” ለማለት እንኳን ሞራል ሳይኖረን አእምሯችንን በአፈ-ታሪክ ብቻ ወጥረን አንዲት ኢንች እንኳን ወደፊት መራመድ እንዳልቻልን ለምን አናስተውልም?
አጼ ምኒሊክ ኢትዮጵያን ግዛት አንድነት ለማስፋፋት ባደረጉት ጦርነት ወንጀል ፈጽመው ከሆነ አጽማቸው ወጥቶ ለፍርድ ይቅረብ ነው የምትሉት?  ወይንስ ይህ ትውልድ የዚያ ወንጀል ውርስ አለበት? ውርስ ካለበትስ ማን ነው ወራሹ? አማራው? ጉራጌው ወይንስ ኦሮሞው?  እንደ ዘረኞች፣ ደም መለካት ካለብን እኚህ መሪ ከአማራም፣ ከኦሮሞም፣ ከጉራጌም ይወለዳሉ። ጠለቅ ብለን ከሄድን ደግሞ ራስ ጎበና ዳጬን በዚያ ስእል ውስጥ እናያለን። ምእራብ እና ደቡብ ኢትዮጵያን በሃይል የያዙና ያስገበሩ የአጼው የጦር መሪ። ራስ ጎበናን ልንጠላቸው እንችል ይሆናል። ኦሮሞነታቸውን ግን ልንክደው አንችልም።   የወንጀል ውርስ በተዋረድ (guilt by association) ውስጥ ከገባን የኦሮሞን ህዝብም በአእምሯችን ለፈጠርነው ወንጀል ወራሽ ልናደርገው ነው።
የቴዲ አፍሮ “ጥቁር ሰው” አልበም የሚያሞግሰው ኢትዮጵያን ከወራሪ ጠላት የታደጉትን ጀግኖች ነው። እነ ፊታውራሪ ሃብተጎርጊስ ዲነግዴን እና እነ ባልቻ አባ ነፍሶ። ቴዲ አፍሮ ለነዚህ ጀግኖች ባያቀነቅንላቸውም ከታሪክ መዝገብ ላይ ልንፍቃቸው አንችልም። የታሪክ ተመራማሪዎች ስለነዚህ ጀግኖች የጻፉት አፈ-ታሪክ ወይንም ድርሰት አይደለም። በጀግኖቹ የምንኮራው በዘራቸው ሳይሆን የሰሩት ገድል ነው። በ’ጥቁሩ ሰው’ የተመራው ይህ የጸረ-ቅኝ ግዛት ገድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው አፍሪካና ለጥቁር ህዝቦች ነጻነት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህ ሊዋጥላችሁ የሚገባ እውነታ ነው። በዚያ ገድል የሚያፍሩ ካሉ የራሳቸው ጉዳይ። መላው የአፍሪካ ህዝብ ግን ይኮራበታል። የአለም ጥቁር ህዝብም ሲያስታውሳቸው ይኖራል።
ዘር እየቆጠርን ከሄድን ብዙ የሚጎረብጡ ነገሮችን ልናነሳ ነው። በግዛት ማስፋፋቱ ሂደት ግን አንድ ሃቅ አለ።  ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ህልቀ መሳፍርት ኢትዮጵያዊ አልቋል። ይህ ደግሞ የድንበር መስፋፋት፤ እድገት እና ስልጣኔ ይዞት የሚመጣው ችግር እንጂ አንድን ህዝብ ለመጨረስ ጥናት ተደርጎ የተሰራ እንዳልሆነ ታሪኩን ከስር መሰረቱ ማየቱ ይበጃል። ችግሩ በእኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በአያሌ ሃገሮች እንደተከሰተ የታሪክ መዛግብት ይነግሩናል። በ17ኛው ክፍለዘመን የተከሰተው የኢንዱስትሪ አብዮት ሳብያ እንኳን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት የማይተናነስ እልቂት ነበር።
አጼ ምኒሊክን ከጀርመኑ ኦቶ ቮን ቢስማርክ ጋር የሚያመሳስሉ ምሁራንም አሉ። እርግጥ ነው ጀርመን  አሁን የያዘችውን ግዛት ቅርጽ እንድትይዝ ያደረገው ፕሩሲያዊው ቢስማርክ ነው። ቢስማርክ የጀርመንን አንድ ታላቅ ኤምፓየር ለመፍጠር አንባገነን፣ ሃይለኛና ጦረኛ መሆን ነበረበት። ታዲያ ይህችን ሃያል ሃገር በመመስረቱ ጀርመኖች አልጠሉትም። ይልቁንም የጀግንነት ስያሜ ለግሰውታል። አያሌ የመታሰቢያ ሃውልቶችንም አቁመውለታል።
ቢስማርክ የህግ ምሁር ነበር። አጼ ምኒሊክ ግን መደበኛም ሆነ ዘመናዊ ትምህርት የተማሩ ሰው አልነበሩም። ከታሪክ እንደምንረዳው በአጼ ልብነድንግል ዘመነ መንግስት፤ የግራኝ አህመድ ወረራን ተከትሎ የነበረውን መከፋፈልና መተላለቅ ለማስቆም መሪዎች ተነሱ። ሃገርን አንድ የማድረጉን ትግል አጼ  ቴዎድሮስ ጀመሩት፣ አጼ ዮሃንስ ቀጠሉበት ከዚያም እምዬ ምኒሊክ ተረከቡት።
አጼ ምኒሊክ ለአመታት በኦነግ ሰዎች ተወግዘዋል። ውግዘቱ አሁንም እታገልለታለው የሚሉትን ህዝብ ችግር ሲፈታው አለየንም። በ1991 ከህወሃት ጋር ጋብቻ ፈጽመው የምኒሊክ ቤተ-መንግስት ሲገቡ ይናገሩት የነበረውን ሁሉ ረሱት። ከቶውንም ያነሱት የነበረው የኦሮሞ ህዝብ የመብት ጉዳይ ሳይሆን የስልጣን ጥያቄ ለመሆኑን አረጋገጡልን።  የሽግግር መንግስቱን ቻርተር ሲያጸድቁ “ኢትዮጵያዊ አይደለንም” የሚለውንም ሳያውቁ ዘንግተውት ነበር። ከገዢው ፓርቲ ጋር የጀመሩት ግዚያዊ ጋብቻ በፍቺ ሲጠናቅቅ የምኒሊክ ጠላትነት መፈክራቸውን እንደገና አነሱት።
የዘር ፖለቲካው ስካር ሞቅ ብሎ በነበረበት በዚያን ወቅት እንደቀልድ ይነገር የነበረ አንድ ቁም ነገር አለ። አንድ የምግብ ቤት በር ላይ በላቲን ፊደል “አማራ መግባት ክልክል ነው!” የሚል ጽሁፍ ሰፍሯል። የጽሁፉ ትርጉም ያልገባው አንድ የአማራ ተወላጅ ጎራ ብሎ ምግብ አዘዘ። አስተናጋጆቹ የሰውየው ድፍረት አስደነገጣቸው። ባለስልጣን ስለመሰላቸው አስተናገደዱት። ዳግም እንዳይመለስም እጥፍ ዋጋ አስከፈሉት። ሰውየው በድጋሚ ሲመጣ ሶስት እጥፍ አስከፈሉት። በሌላ ግዜ ከአምስት ጓደኞቹ ጋር መጥቶ ምግብ አዘዘ። ከተስተናገደ በኋላም አራት እጥፍ ቢል አቀረቡለት።  በዚህ ግዜ ቲፕም ጨምሮ ሰጣቸው።  የሆቴሉ ባለቤት በነጋታው “አማራ መግባት ክልክል ነው!” የሚለውን ጽሁፍ አንስቶ “ኦሮሞ መግባት ክልክል ነው!” በሚል ቀየረው።
በአሁኑ ዘመን ከበድ አለ እንጂ፣ ሰዎችን በጎሳ አደራጅቶ ከማሳደም የቀለለ ትግል የለም። ደም ከውሃ ይወፍራል እንዲሉ፤ ሰዎች በጋራ የሚጋሩትን ነገር እያነሱ ስነልቦናዊ ዘመቻ ማድረግ ስኬት ሊኖረው ይችላል። ዘለቄታ ግን አይኖረውም። የዘር ፖለቲካ ልክ እንደ ስካር ነው። ይሞቃል ከዚያም ይበርዳል። በርግጥ በሞቅታ ግዜ የሚፈጠረው አደጋ ቀላል ላይሆን ይችላል። እ.ኤ.አ. በ1993 በምስራቅና በምእራብ ኢትዮጵያ የተፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል ለዚህ ዋቢ ነው። የኦነግ ልሂቃን የ19ኛውን ክፍለ ዘመን ጉዳይ እየደጋገሙ ያነሱልናል።  በ21ኛው ክፍለ ዘመን በራሳቸው እጅ የተፈጸመው ግድያ ግን በብሄራዊ ቴሌቭዥን ጭምር እንድናየው ተደርጓል። ነብሰ-ጡር ሴቶች በጩቤ ሆዳቸውን እየተሰነጠቁ ሲገደሉ አየን። ነብስ ያላወቁ ሕጻናትና የ90 አመት አዛውንት ጭምር ከተራራ ላይ እየተወረወሩ ሲጣሉም የአይን ምስክሮች ነን። እነዚህ ሰዎች የምናስታውሰው ይህን በመሰለ ወንጀል ብቻ አይደለም። ድርጊቱ የቂምና የቁርሾ አሻራ ጥሎ አልፏል።
ይህ ሁሉ በደል በዘመናችን ተፈጸመ። በዳዮቹ ግን አሁንም በቀልን አርግዘው ይጓዛሉ።
የበደሌ ቢራን አለመጠጣት የኦሮሞን ችግር የሚፈታ ከሆነ፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ቢራውን መጠጣት ያቁም። የአኖሌን ሃውልት መሰራት ለኦሮሞ ህዝብ ፍትህ የሚያመጣ ከሆነ ደግሞ፤ ሃውልቱ በየከተማው ይገንባ። ግና ይህ ሃውልት ለመጭው ትውልድ ጥሎት የሚያልፈው ቂምና በቀልን እንጂ፤ ለሚታገሉለት ህዝብ የፍትህ ጥያቄ ዋስትናው ምን እንደሆነ ልንረዳው አልቻልንም። አሁን ያለው ትውልድ ያልፋል። ከዚህ ትውልድ በኋላ ለሚወለዱት ልጆች ጥለንላቸው የምናልፈው ቅርስ ጥላቻ፣ ቂም እና በቀል ብቻ ይሆናል።
ከዘመናችን ታላቅ ሰው ከኔልሰን ማንዴላ አንድ ነገር እንማር። ማንዴላ የደቡብ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን የአለምን ፖለቲካ የለወጠ የፖለቲካ ነብይ ነው። ይህንን ሲያደርግ የፖለቲካ ፎርሙላ አልነበረውም። ክፉን ነገር በበጎ ለማሸነፍ ወሰነ። ጥላቻን በፍቅር ለወጠ። ልክ እንደ ክርስቶስ፣ የበደሉትን ሁሉ ይቅር ብሎ በፍቅር አሸነፋቸው። ታሪክ ሰርቶ አለፈ። ስሙም ከመቃብር በላይ ለዘልአለሙ ይኖራል።

Wednesday, December 11, 2013

ከተወዳጁን ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ Interview with Teddy Afro [Enqu Magazine]

(እንቁ መጽሔት) ተወዳጁን ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁንን በዚህ የመጽሔታችን ልዩ ዕትም፤ የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን 100ኛ የሙት ዓመት… በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለመከበሩን ጉዳይ በተመለከተ ጥያቄዎች አቅርበንለታል። ቴዲም በምላሹ “በማንኛውም ሁኔታ ጥሩ የሠራን ሰው ማመስገን፣ ማክበር ጠቃሚ ባህል መሆኑን ተረድተን፤ በዚህ በኩል እስከዛሬ ያለውን ስሕተት ማረም አለብን” ብሏል። ሌሎች መሰል ሐሰብ አስተያቶችንም ሰንዝሯል። ሁሉንም ከቃለ-ምልልሱ ዝርዝር ይዘት ያገኙታል። መልካም ቆይታ!
ዕንቁ፡- የዳግማዊ ዐፄ ምንሊክ 100ኛ የሙት ዓመት በብሔራዊ ደረጃ አለመከበሩን እንዴት አየኸው?
ቴድዎሮስ፡- በቅድሚያ ከአከባበሩ አግባብነት ተነስተን ለይተን ልናስቀምጠው የሚገባ ነጥብ መኖር አለበት። ይከበራል የሚባለው ቀን የሞቱበት ይሁን፤ ሥርዓተ ቀብራቸው የተፈጸመበት ወይስ ምኒሊክ በሠሯቸው አገራዊ ቁም ነገሮች ላይ ያአተኮረ ይሁን የሚለው ሀሳብ እራሱን የቻለ ውይይት የሚፈልግ ነው። እንዲህም ሆኖ ግን በግሌ የምኒልክ ማንነትም ይሁን ለኢትዮጵያ ያበረከቱት አስተዋፅኦ በብሔራዊ ደረጃ አለመከበሩ ያሳስበኛል።
ዕንቁ፡- በአንተ ግንዛቤ ከኢትዮጵያ ባሻገር ባለው ዓለም ብሔራዊ ኩራት የሆኑ ሰዎች ስለምንድነው የሚታሰቡት? አያይዘህም ምኒልክን በማክበር ሊገኝ ይችላል ብለህ የምታምንበትን ብሔራዊ ጥቅም ብትገልጽልን?
ቴድዎሮስ፡- ግለሰቦች እንዲታወሱ የሚደረግበትም ምክንያት፤ መሻሻልና መደገም ያለባቸው ጥሩ ታሪኮች ወደ አዲሱ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ስለሚፈለግ ነው። እነዛ ብሔራዊ ኩራት መሆን የቻሉ ሰዎች ሲታሰቡ ወይም የመልካም ስምና ተግባራቸው ማስታወሻ ዝግጅት ተደርጎ ክብራቸው እንዲገለጥ ሲደረግ፤ ሌሎች መልካም የሚሠሩ ሰዎችን ማፍራት የሚያስችል መነሣሣትን ይፈጥራል። በመሆኑም ነው ክብረ በዓሎች በታላላቅ ግለሰቦች ስም እየተሰየሙ፣ የእነሱም መልካምነት እየታሰበ የሚወሱበት አንድ ብሔራዊ ዝግጅት የሚከናወንበት ሥርዓት የሚያስፈልገው።
ዕንቁ፡- ዳግማዊ ምኒልክ ስለዛሬይቱ ኢትዮጵያ መፈጠር ሲሉ የገቡበትን ጦርነት እንዴት ነው የምትመለከተው?
ቴዎድሮስ፡- ምንጊዜም ሰዎች የሚበጃቸውን ነገር እስኪገነዘቡት ድረስ ያለመግባባቱ መጠን ይሰፋል። ያም ግጭት ሊፈጥር ይችላል። ይህም ደግሞ በእኛ ሀገር ሁኔታ ብቻ የተከሰተ ሳይሆን በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሆነም ነው። እንዲህም ሆኖ ግን ለምሳሌ ምኒልክ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ዘምተው ንጉሥ ጦናን ማረኩ። ከማረኳቸውም በኋላ እግራቸውን እያጠቡ ‹‹የእኛ አንድ አለመሆን፣ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት አለመመሥረታችን፤ የጋራ ለሚሆነው ጠላታችን ጥቃት አሳልፎ የሚሰጠን አደገኛ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። በዚህ ምክንያት ነው ወደ አንተ ጦር ያዘመትኩት እንጂ ሥልጣንህን ለመቀማትና በአንተ ላይ ለመግነን… ፈልጌ አይደለም። ማእከላዊ መንግሥታችንን ማጠናከሩ ግን ሁላችንንም የሚጠቅመን ነው። አገራችንን፣ በሕላችንን፣ ታሪካችንን፣ ቋንቋችንን ጠብቀንና ድንበራችንን አስከብረን ለመኖር ይረዳናል›› ነበር ያሏቸው።
ለምንጊዜውም ነገሮችን በቀና ማየትና የጎደለውን ሞልቶ፣ ያለውን ጥሩ ነገር እንዳለ ይዞ መሄዱ፤ ለተሻለ ሀገራዊ ርምጃ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህን የመሰለው አካሄድ ደግሞ በሌሎች አገሮች አልተሠራበትም የሚል ቅንጣት ዕምነትም የለኝም። ወቅቱ በረዳቸው መጠን የነበረውን የአንድነት ክፍተት ሞልተውና አመጣጥነው ማእከላዊ መንግሥቱን ከነበረው የግንዛቤ ማነስ ሁሉ… ቀድመው፤ በተቻለ መጠን በትህትና ዝቅ ብለው እግር በማጠብ ጭምር የነበረውን መጥፎ ሁኔታ መልክ ለማስያዝ ደክመዋል። ዛሬ ያለው ኢትዮጰያዊም ከተለያየ የኢትዮጵያ ብሔሮች ምንጭ ፈልቆ ይኸው በአንድነት ‹‹ኢትዮጵያዊያን ነን›› ለማለት ችሏል። ስለዚህ የምኒልክ ስም ብሔራዊ አክብሮት ማግኘት የሚገባው፣ በሕልውናችንም ላይ ከፍተኛ የሆነ ሚና ያለው፣ የተባበታተነውን ሰብስበው ያቆዩ በመሆናቸው ነው።
ዕንቁ፡- “በዐፄ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት የተጀመሩት ሥልጣኔን የመከተል ጉዞዎች እንደጅምራቸው ቀጥለው ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ያደጉትን ሀገራት ጎራ ለመቀላቀል በቻለች ነበር” በማለት የሚቆጩ ወገኖች አሉ። አንተስ ምን ትላለህ?
ቴዎድሮስ፡- ያንን የሥልጣኔ ጅምር ከነበረው የኋላቀርነት ሁኔታ ጋር ሲመለከቱት ለመቀበል በጣም ከባድ ነበር። ለምሣሌ ‹‹ ስልክ ማነጋገር የሰይጣን ተግባር ነው…›› በማለት የተቃውሞ ሃሳባቸውን የሚሰነዝሩ ሰዎች ነበሩ። እንደዚህ ያለውን አመለካከት እና አስተሳሰብ አሸንፎ ለመሄድ ምኒልክ ብዙ ደክመዋል። ከዚህ ተነስተን የመሄዱ ጉዳይ በእሳቸው ተነሳሽነትና አስተማሪነት የተጀመረ ቢሆንም ቀዳማዊ ሀይለስላሴ በስልጣን ዘመናቸው ትምህርትን በማስፋፋት የተወሰነ ደረጃ ለማስኬድ መሞከራቸው የስልጣኔ ምንጩ ትምህርት መሆኑን ያገናዘበ ቀጣይ እርምጃ ነው ለማለት ያስደፍራል።
ዕንቁ፡- አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ባለታሪክ የሆኑ አርዓያዎቻቸውን ያለማክበራቸው ችግር ከምን የመነጨ ነው?
ቴዎድሮስ፡- የችግሩን ምንጭ አጠር አድርጎ ለመግለጽ ያስቸግራል። ነገር ግን ምንግዜም ቢሆን ለጥሩም ይሁን ለመጥፎው ድርጊት፤ መንግሥትም በመንግሥትነቱ፣ ሕዝቡም በሕዝብነቱ የየራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል። እንዲያም ሆኖ ለሀገርና ለወገን የሠራን ሰው ማክበር ጠቃሚ ባሕል ነው። ምንግዜም ቢሆን ጥሩ ተምሳሌት በማይኖረው ማኅበረሰብ ውስጥ ጥሩ የሚሰራ ዜጋ ለማፍራት አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ በማንኛውም ሁኔታ ጥሩ የሠራን ሰው ማመስገን፣ ማክበር ጠቃሚ ባህል መሆኑን ተረድተን፤ በዚህ በኩል እስከዛሬ ያለውን ስሕተት ማረም አለብን። ጥሩን ነገር ማየትና ማክበር መቻል፤ ጥሩ ነገር በራስ ውስጥ እንዲሰርጽ መፍቀድ ማለት ስለሆነ፤ ከሞቱት ሰዎች ሕይወት ያለው ሥራቸዉን ወስዶ መራመድ የሚገባን ይመስለኛል።
ዕንቁ፡- እስቲ “ምኒልክ ተወልዶ…” ስለሚባልበት ምክንያት የሚሰማህን ግለጽልን?
ቴድዎሮስ፡- አዎ ‹‹ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፣ ግብሩ ዕንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ›› ተብሏል። ለእኔ ዕንቁላሉ የምዕራባውያንን ባሕልና ቋንቋ፣ በመውሰድ የራስን ባህል እና ማንነት ለማስጣል የተሞከረውን ሀሳብ ይወክላል።ዕንቁላሉ ውስጥ ተደብቆ የመጣው የተገዥነት አስኳል ሌላው ምስጢር ነው። የዚህ ጥቅስ ወርቁ በራሱ ባለብዙ ትርጉም ነው። ምኒልክ በራስ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ፍልስፍና… የመመራት አስተሳሰብ እንዳይጠፋ ያደረጉትን አስተዋፆም ደርቦ ይገልፃል።
ዕንቁ፡- “የምኒልክ ታላቅነት መከበር የነበረበት በኢትዮጵያ ብቻ አልነበረም። በአፍሪካም ደረጃም ነው እንጂ” የሚሉ ወገኖች አሉ። ለዚህም አባባላቸው አስረጅ የሚያደረጉት የዓድዋን ድልና የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎውን ነው። የአንተ እስተያየትስ?
ቴዎድሮስ፡- በስፋት እንደሚታወቀው የዓደዋ ድል፤ ለመላው አፍሪካውያን ወንድሞቻችን…. ነጻ መውጣት ታላቅ የሞራል ስንቅ መሆን የቻለ ነው። የኢትዮጵያ አርበኞች ትግል ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበረው የመሰከረ ነው። ነገር ግን ይህን ታሪክ አፍሪካዊ በዓል አሳክለን ከማክበራችን በፊት ትርጉሙን ባገናዘበ መልኩ ኢትዮጵያዊ በዓል አክሎስ ይከበራል ወይ የሚለዉን ጥያቄ በቅድሚያ ለራሳችን መመለስ ያለብን ይመስለኛል።
ዕንቁ፡- ከዚሁ ወቅታዊነት ያለው ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ይኖረዋል የሚል ግምት አለንና … “ጥቁር ሰው ” የተሰኘውን ዜማ ለመሥራት ምን አነሣሣህ?
ቴዎድሮስ፡- አንድ ሰው ከፍላጎቱ፣ በውስጡ ከሚፈጠረው ስሜትና ከተፈጥሮአዊ ዝንባሌው በመነሳት ሥራዎችን ይሠራል። አንድ ሰው ማንን ይመስላል? ቢባል፤ እናቱንም አባቱንም ከመምሰሉ በላይ አነጋገሩን ይመስላል እንደሚባለው እኔም የምጫወተው ሙዚቃ የምናገረውን ይመስላል ማለት ነው። ከምንምና ከመቼውም ጊዜ በላይ ለእነዚያ ታሪክ የሠሩ ሰዎች አክብሮት መጠስት ተገቢ ነው የሚል ስሜት በውስጤ ይመላለስ ስለነበር፤ ያንን ስሜት ለመግለፅ ስል የሠራሁት ሙዚቃ ነው።
ለምሣሌ የምኒልክ ተግባር ዛሬ ያለንበትን ሀገር መዋቅር የሠራ በመሆኑ፤ የተዘፈነው ዘፈን ለክብራቸው ቢያንስ እንጂ የሚበዛ ሊሆን አይችልም። እንዲህም ሆኖ መቼም የሰው ልጆች አመለከካከት እና ስሜት የተለያየ ስለሆነ ዳግማዊ ሚኒልክ ያበላሹት ተግባር አለ ብለን የምናምን ወገኖች ካለን እንኳ የተበላሸውን ነገር ለማስተካከል በተበላሸ መንገድ መሄድ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። በተበላሸው መንገድ የሚኬድ ከሆነ ምንጊዜም በዚህ ምድር ላይ ዕዳ ተከፍሎ ሊያልቅ አይችልም።ዕዳ ተከፍሎ የሚያልቀው በፍቅር ብቻ ነው። ጥቁር ሰውንም የፈጠረው ‹‹ፍቅር ያሸንፋል›› የሚለው መንፈስ ነው። ። በዳህላክም ላይ የምናየው ይሄንኑ ነው። ስለዚህ ዕዳ የመሰረዝ ጉዳይ ከአበዳሪ አገሮች የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከእየራሳችንም ህሊና የሚጠበቅ ተግባር ነዉ።
ዕንቁ፡- የምኒልክ የመሪነት ጥንካሬ ከራሳቸው ብቻም ሳይሆን ከዕተጌ ጣይቱም አጋርነት የሚመነጭ ስለመሆኑ የታሪክ መዛግብት ላይ ሠፍሮ ይነበባል። አንተስ ስለጣይቱ ምን ትላለህ?
ቴዎድሮስ፡- ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጀርባ አንዲት ሴት አለች እንደሚባለው የምኒልክ ጥንካሬ የጣይቱም ነው። ከዚህም በዘለለ ልናየው ስንሞክር የጣይቱ ሚና ሲመዘን አንደኛ የምኒልክን የልብ ሥፋት የምንረዳበት ነው። በጊዜው እንደማንኛውም ኋላቀር አስተሳሰብ ለሴቶች ከሚሰጠው ግምት አንፃር ምኒልክ ሚስታቸውን በነበሩበት ደረጃ ኃላፊነት የሰጡ፣ ምክራቸውንም ለመቀበል የማያመነቱ ሰው ሆነው እናገኛቸዋለን። ዛሬ ስለሴቶች ጥንካሬ ለማወራት፤ ጣይቱ በጣም ጥሩ ምሣሌ ናቸው። ይሄ የጣይቱ ብልሀት፣ የጣይቱ መንፈሳዊ ጥንካሬ፣ የአመለካከት ሥፋትና ጥልቀት… ምኒልክን ‹‹ዕምዬ›› እስከማሰኘትና አልፎ ተርፎም በዓድዋ ጀግንነታቸው ጎልቶ እንዲዋጣ የወኔ ኃይል እስከመሆን ደረጃ የዘለቀ ነው። የሁለቱ የመቻቻልና የመደማመጥ መጠን በራሱ፤ በተለይ አሁን አሁን… ለሚስተዋለውና ‹‹የሴቶች የበታችነት፣ የወንዶች የበላይነት…›› ለሚባለው አጀንዳ ጥሩ ማጣቀሻ ነው። ከዚህም ባሸገር ጣይቱ በብዙ መመዘኛ ትልቅ ሥራ የሠሩ ሴት ናቸው።
ዕንቁ፡- ምኒልክን በተመለከተ እንደ ሙዚቃው ሁሉ ፊልም ሠርቶ ሕያው ሥራዎቻቸውን ማክበር አይቻልም?
ቴድዎሮስ፡- አንተ ያላከበርከውን ሌላው ሊያከብርልህ አይችልም። አፍሪካዊያን ወገኖቻችን የእኛን አባቶችና አያቶች ዋጋ ያውቃሉ። እኛ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ላይ ለመድረስ ገና ጭቅጭቃችንን አልጨረስንም። ስለዚህ በፊልምም ሆነ በሙዜቃ መደገፎ ጠቃሚነቱ በአያጠያይቅም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እኛ በታሪካችን ላይ ያለንን ግንዛቤ የማስፋት ደረጃና ጥልቀቱ በቂ ሆኖ መገኘቱ ላይ ነው።
ዕንቁ፡- የምኒልክ ማንነት በብሔራዊ ደረጃ መከበር ይገበዋል… ከመባሉ አኳያ ለወጣቱ ትውልድ የምታስተላልፈው መልዕክት ይኖርሃል?
ቴዎድሮስ፡- ቅንነት ከሌለ ጥሩ ነገር ማየት እንደማይቻል አውቆ። ታሪኩንም በቅንነት ስሜት መመርመር ይኖርበታል። የባለታሪክ ሰዎችን ጥሩ ነገር መውሰድና ጥሩ ያልሆነ ነገራቸውን ደግሞ እንዳይደገም ለማረም መትጋት ከኛ ከወጣቱች ይጠበቃል። ትልቁና ቁልፍ ነገር የማንነትን መሠረታዊ ጥያቄ ከመገንዘብ ይመነጫል። ሕይወትም የሚጀምረው ራስን ከመሆን ነው። ሰው ራሱን ሲያክል ሌላ ብዙ ነገር ማድረግ ይቻለዋል።… ስለዚህ የነገር ሁሎ ምንጭ ፍቅር ስለሆነ ከፍቅር የሚጀምረውን ህይወት በፍቅር ለመጨረስ ቅንነት ያስፈልጋል። አመጣጡን ያዬ አካሄዱን ያዉቃልው ምክኒያቱም ታሪኩን እየዞረ የማያይ ተጋዥ የኋላ መመልከቻ መስታወት የሌለው መኪናን ይመስላልና።